የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እያነቃቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እያነቃቃ ነው
ደሴ ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ላሊበላን ጨምሮ በምስራቅ አማራ ለሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ማዕከል በመሆን ለአካባቢው ቱሪዝም መነቃቃት ዕድል መፍጠሩ ተገለጸ።
በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን በማልማት አካባቢውን የምስራቅ አማራ የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በ"ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት ተገንብቶ አገልግሎት የጀመረው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ከሰሜን ሸዋ እስከ ላሊበላ ድረስ የሚገኙ ለእይታ ሳቢ የሆኑ መልክዓ-ምድርና ታሪካዊ ስፍራዎችን በማስተሳሰር፣ ምስራቅ አማራ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን መልካም ዕድልን ይዞ መጥቷል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን ሲጎበኙ ያገኘናቸው አቶ መስፍን አያሌው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የሪዞርቱ ግንባታና አሰራር ከሐይቁ ተፈጥሯዊ ይዘት ጋር ተዳምሮ የሚያስደምምና ቀልብን የሚገዛ ነው።
የሪዞርቱ መመረቅ በሚዲያ ከመስማት ውጭ በአካል ሄዶ የመጎብኘት ዕድል እንዳላጋጠማቸው የገለጹት አቶ መስፍን፣ አሁን ሐይቁንና ሪዞርቱን በመጎብኘታቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ሪዞርቱ ከሐይቁና በአካባቢው ካለው ማራኪ መልክዓ-ምድር ጋር ተዳምሮ ምቹ የመዝናኛ ስፍራ በመሆን ለምስራቅ አማራ ቱሪዝም መነቃቃት ትልቅ ዕድልን የፈጠረ መሆኑንም አክለዋል።
ሌላዋ ጎብኚ ወይዘሮ ዘቢብ ሁሴን በበኩላቸው፤ የሪዞርቱ መገንባት ለእይታ ግልጽ ያልነበሩ በሐይቁና በዙሪያው የሚገኙ እምቅ ጸጋዎች አሁን ተገልጠው የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።
"ሪዞርቱ ከአካባቢው ውብ ገጽታ ጋር ተዳምሮ ምቹ የመዝናኛ አካባቢ በመፍጠሩ ልጆቼን በመያዝ እየጎበኘንና እየተዝናናን እንገኛለን" ብለዋል።
ሪዞርቱ እጅግ ሳቢና ማራኪ ሆኖ መገንባቱን እና በጉብኝታቸውም መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የሪዞርቱ ጎብኚ አቶ አህመድ ሰይድ ናቸው።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም አበበ በበኩላቸው፤ የሪዞርቱ መገንባት የአካባቢውን ሀብት ገልጦ በማሳየት የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ማስቻሉን አስረድተዋል።
ለአካባቢው ምቹ የመዝናኛና የስብሰባ ማዕከል ከመሆን ባሻገር፣ በግቢው ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው የፍራፍሬ ልማት አካባቢውን የምርምር ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን ከሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ጋር በማስተሳሰር ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አስያ ኢሳ ናቸው።
የሎጎ ሐይቅና ሪዞርት ከደሴ ወደ ሰሜኑና ወደ ምስራቁ የአፋር ክፍል ለመጎብኘት ፍላጎት ለሚኖራቸው የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።
በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች፣ የስፓ አገልግሎት፣ የመዋኛ ገንዳዎች እንዲሁም የውስጥና የውጭ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን አካቶ የያዘ ነው።