የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) የአፍሪካ ሀገራት በመካከላቸው የሚያካሂዱትን ንግድ በማሳለጥ፣ የንግድ እንቅፋቶችንና ታሪፎችን በመቀነስ አንድ የተቀናጀ የአፍሪካ የንግድ ገበያ ለመፍጠር የታቀደ የአህጉሪቱ የንግድ ማዕቀፍ ነው።
ዋና ዓላማዎቹም በአፍሪካ መካከል የሚደረግን ንግድ ማሳደግ፣ የጉምሩክ ታሪፎችንና ሌሎች የንግድ እንቅፋቶችን መቀነስ፣ የአፍሪካን የእሴት ሰንሰለቶች ማጠናከር እና የአፍሪካ ምርቶች በአህጉሪቱ ውስጥ በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ናቸው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የንግድ መድረኮች አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ እና ከ3.5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ አቅም ያላት በመሆኗ ከፍተኛ ገበያን እንደምትወክል ጠቁመዋል።
ነገር ግን በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚካሄደው የአህጉር ውስጥ ንግድ መጠን ከአፍሪካ አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ ከ18 በመቶ ያነሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ከአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ከአህጉሩ ውጪ ካሉ ሀገራት ጋር የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካ የራሷን ገበያ፣ ዕድሎች እና አቅም እስካሁን በሙሉ አቅም እንዳልተጠቀመችበት ገልጸው፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ገበያ የአፍሪካ ሀገራትን ማቀራረብ የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
ከ2018 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ የአፍሪካ ሀገራት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለመመሥረትና ወደ ሥራ ለማስገባት በአንድነት መቆማቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዷን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ምርቶችን ወደ በርካታ ሀገራት በመላክ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ ወደ ውጭ ገበያ ለመግባት የሚያስችሉ በቂ መድረኮች ስላልነበሩትና በአብዛኛው በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ተወስኖ ስለቆየ፣ በተዘጋ አካባቢ ውስጥ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ በብቃት ለመሳተፍ ያላትን አጠቃላይ ዝግጁነት ለማሻሻል ከተለያዩ ተቋማት፣ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰፊ የክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ኢትዮጵያ ወደ ሰፊው ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት መዋሃድ የጀመረችበት ዋና መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምርቶች በየትኛውም ገበያ ተፈላጊ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎች ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ሰፋፊ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።