የአዲስ አበባ ፈጣን ለውጥ ለአደባባይ በዓላት ድምቀት እና ለቱሪዝም ዕድገት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፈጣን ለውጥ ለአደባባይ በዓላት ድምቀት እና ለቱሪዝም ዕድገት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የኮሪደርና ሌሎች ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች እንደ መስቀል፣ ኢሬቻ እና የዒድ አልፈጥር ሶላት ያሉ የአደባባይ በዓላትን በድምቀት ለማክበር እና ለቱሪዝም ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ፣ በወንዝ ዳርቻዎች ፣ በዘመናዊ መናፈሻዎች፣ በስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች እና በሌሎችም ሁለገብ ስራዎች እጅግ ፈጣን እና አስደናቂ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።
እነዚህ ተጨባጭ የልማት ስራዎች መዲናችንን በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ከማድረጉም በላይ፣ የሀገራችንን ገጽታ በእጅጉ ቀይረውታል።
ከተማዋ አሁን ላይ የያዘችው ማራኪ ገጽታና ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በአደባባይ ለሚከበሩ የተለያዩ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በዓላት ልዩ ድምቀት አጎናጽፈዋል።
ይህም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር የሚመጡ ቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ነመራ በርሲሳ፤ ዘንድሮ በመዲናዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በርካታ መሠረተ ልማቶች በተገነቡበት ወቅት መከበራቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።
እነዚህ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች በዓላቱን በድምቀት ለማክበር ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመው በእነዚህ ወቅቶች ለመሠረተ ልማቶቹ ደህንነት ትኩረት በመስጠት መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑት እና እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች ከአካባቢ ጥበቃ እና ከፅዳት አንጻር እጅግ የተሻሻሉና ለማህበረሰቡ ምቹ ሁኔታን የፈጠሩ መሆናቸውን ያብራሩት ደግሞ ወይዘሮ ወገኔ ኃይሌ ናቸው።
ኮሪደርን ጨምሮ በመዲናዋ የተገነቡት መሰረተ ልማቶች በዓላቱን ለመታደምም ሆነ ለጉብኝት ወደ መዲናዋ የሚመጡ ጎብኚዎች በሚመለከቱት እና በሚያገኙት ጥሩ መስተናግዶ ተደስተው እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ፍቅሩ እንዳለው፤ በበኩሉ በአዲስ አበባ የተሰሩ የልማት ሥራዎች ከተማዋ የአፍሪካ መዲና መሆኗን በተጨባጭ የሚያስመሰክሩ ናቸው ብለዋል።
ይህም በዓላቱን የሚታደመው ህዝብ እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እንደ ልባቸው ተዝናንተውና ተደስተው የሚመለሱባት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።
አቶ መስፍን ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ የበዓላትና የቱሪስት ፍሰቱን በሚመጥን መልኩ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች በዓላቱን በጥሩ መንፈስ ለማክበር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ የተገነቡ አዳዲስ የልማት ስራዎች የሀገሪቱ መልካም ገጽታ በላቀ ደረጃ ጎልቶ እንዲታይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ጠቁመዋል።
አቶ ፀሃይ መላኩ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል አዲስ አበባ የነበራት የፅዳትና የውበት ሁኔታ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው በዓላትን ምቹ እና ደማቅ በሆነ መልኩ ለማክበር አስቸጋሪ ነበር ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ግን በከተማዋ በተከናወኑ የኮሪደር እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አዲስ አበባ እጅግ ውብ፣ ፅዱና ማራኪ በመሆኗ በዓላቱን ደስ በሚል መልኩ ማክበር እንችላለን ነው ያሉት።
ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ ማሪያ አንጋ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ይህም ዘንድሮ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትን ከምንጊዜውም በላይ ለየት ባለ እና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።