የባህር በር ባለቤትነት ቀጣናዊ ደህንነትን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ባለቤትነት ቀጣናዊ ደህንነትን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ደህንነትን የማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የማፋጠን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሃምዛ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከዓለም ጋር የምትገናኝባቸው የባሕር በርና የባሕር ዳርቻ መዳረሻ ወደብ ባለቤት እንደነበረች በታሪክ ተሰንዶ ይገኛል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ ስትወጣ፣ ኢትዮጵያ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን በማጣቷ የባህር በር አልባ ሀገር ሆናለች።
የባህር በር የውጭ ንግድን ለማፋጠን፣ የወጪና ገቢ እቃዎችን የማጓጓዣ ወጪ ለመቀነስና የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ ወሳኝ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብትና ቀጣናዊ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ከባህር በር ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሃምዛ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የነበራትን የባህር በር ያጣችው በራሷ ልጆች ስህተትና በውጭ ኃይሎች የተቀናበረ ሴራ ነው።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፈ የጎረቤት አገራትን ተጠቃሚነትም ያረጋገጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንትም ጀምሮ የአፍሪካ የነጻነት፣ የሰላምና የደህንነት ተምሳሌት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ እምቅ አቅም አላት ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ከቀጣናው ፖለቲካ መረጋጋትና ሰላም ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዊ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የሀገሪቱን ዲፕሎማሲና ተጽእኖ ፈጣሪነት ከማሳደግ አንጻር ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ አንድነትን ማጠናከርና በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።