ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ያነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ያነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች
ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በኃላፊነት ታዘጋጃለች፤
ጉባኤው የግሉን ዘርፍ እና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ እንዲሁም ውጤታማ መፍትሔ የሚያመጣ እንዲሆን ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ትሠራለች፤
ፕሬዝዳንቱ ሁሉም የዓለም መሪዎች በጉባኤው ላይ በመሳተፍ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል፤
ኢትዮጵያ እየገነባችው ላለው ጠንካራ ኢኮኖሚ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር ያስፈልጋታል፤
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ለሁሉም የቀጣናው ሀገራት ከሚያስገኘው የጋራ ጥቅም፣ ትብብርና ዕድገት አንጻር ሊታይ ይገባል፤
ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን ለማሳካትና ከዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ጋር በጥብቅ ለመተሳሰር ሁሉንም የዲፕሎማሲ አማራጮች ተጠቅማ እየሠራች ትገኛለች፤
1 ነጥብ 6 ቢሊዮን አፍሪካውያን እኩል ውክልና የማግኘት መብት ለዘመናት መነፈጋቸውን እንዴት የዓለም ህሊና ሊቀበለው ይችላል?
የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ሪፎርም ማድረግ የትውልዱ የእውነትና የሞራል ጥያቄ ነው፤
ድርጅቱ የዓለምን ነባራዊ እውነታ ያገነዘበ፣ በፍትሕና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መሠረታዊ ሪፎርም በማድረግ ወቅታዊ የዓለም ፈተናዎችን በተሻለ አቅም መወጣት አለበት፤
ኢትዮጵያ የሰዎች ሰብአዊ ክብር እንዲጠበቅ፣ ፍትሕ እንዲሰፍንና የነፃ ሕዝቦች አብሮነት እንዲከበር ባላት ታሪካዊ ቁርጠኝነት ጸንታ ትቀጥላለች፤
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በውሃ ሀብት የጋራ ቀጣናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያሳየ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፤
ኢትዮጵያ እስከ እ.ኤ.አ. 2030 ተጨማሪ 13,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የምሥራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ገበያ ፍላጎት ለማሟላት አቅዳ እየሠራች ትገኛለች፤
ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በንግድ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር እየሠራች ነው፤
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አለመረጋጋት ለመፍጠር የሚሠሩ የውጭ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፤
ታዳጊ ሀገራት የቴክኖሎጂ አብዮቱ ተመልካች ሳይሆኑ ባለቤት መሆን አለባቸው፤
የኢትዮጵያ የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" መርሃ ግብር እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ አፍሪካ ለቴክኖሎጂው ዘመን ዝግጁ መሆኗን ማሳያ ነው
ባለፉት 8 ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 56 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንና ይህም በዓመት 9 ቢሊዮን ቶን ካርቦን የማመቅ አቅም ይኖራቸዋል፤
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስንዴ አስመጪነት ወጥታ በአፍሪካ ከሚገኙ ትላልቅ የስንዴ አምራች ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች፤
በምግብ ዋስትና ረገድም ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገብ ችላለች፤
የአየር ንብረት ለውጥን የሚያቋቁሙ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን በስፋት በመጠቀም ረገድ አበረታች ስኬት አስመዝግባለች፤
የምግብ አቅርቦት የፖለቲካ አጀንዳ በሆነበት እና የዓለም የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት በተፈተነበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርታማነት አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል ማሳያ ሆኗል፤