የጉራጌ መስቀል- 'ከወሬት የኸና' እስከ 'አዳብና' - ኢዜአ አማርኛ
የጉራጌ መስቀል- 'ከወሬት የኸና' እስከ 'አዳብና'
የጉራጌ መስቀል- 'ከወሬት የኸና' እስከ 'አዳብና'
(በእንዳልካቸው ደሳለኝ ከኢዜአ ወልቂጤ ቅርንጫፍ)
በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ታላላቅና ደማቅ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል መስቀል ይጠቀሳል። የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ቢሆንም በተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ በቤተ ጉራጌ መስቀል ከሃይማኖታዊ ሥርዓት ባሻገር ሰፊ ማህበራዊ ክዋኔ ያለው ሲሆን፣ የተቀያየመ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ ወዳጅና ዘመድ የሚገናኝበት፣ ጋብቻ የሚፈፀምበት እንዲሁም የፍቅርና የአንድነት ማንፀባረቂያ ነው።
በዓሉ በዋናነት በቤተ ጉራጌዎች መስከረም 15 ቀን የሚከበር ቢሆንም፣ የዝግጅት ሂደቱና አከባበሩ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ድረስ የተዘረጋ ረጅም የደስታና የምስጋና ወቅት ነው።
የመስቀል ዝግጅት በይፋ የሚጀምረው ነሐሴ 12 ቀን እንደሆነ የሚናገሩት የሀገር ሽማግሌ አቶ በለጠ ወልዴ፣ በዚህ ዕለት የዓመቱ የመስቀል ደመራ የሚቆምበት እንደሆነ ያብራራሉ። ከዚህ ዕለት ጀምሮ በቤተሰቡ ውስጥ የሥራ ክፍፍል ተደርጎ አጠቃላይ የዝግጅት እንቅስቃሴው ይፋ ይሆናል።
በዚህም መሰረት የስራ ኃላፊነቶችን ሲጠቅሱ፤ ልጃገረዶች የቤቱን የውስጥ ክፍል ማፅዳት፣ በባህላዊ ቀለማትና ጌጣጌጦች ቤት ማስዋብ እንዲሁም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያዘጋጃሉ። የወጣት ወንዶች ዋነኛ ኃላፊነት ደግሞ ጀፎረን በማስዋብ አጥር ማጠር፣ ለበዓሉ የሚሆን የማገዶ እንጨት ማዘጋጀትና ለደመራ የሚሆኑ እንጨቶችን አስቀድሞ ማደራጀት ነው።
አባወራዎች ለበዓሉ የእርድ ሰንጋዎችን የመግዛትና የማዘጋጀት ኃላፊነት ሲኖርባቸው፤ የእናቶች ድርሻ ደግሞ ለባህላዊ ምግቦች የሚያስፈልጉ እንደ ቆጮ፣ ቡላ፣ አይብ፣ ቅቤ እና የመገልገያ ባህላዊ ቁሳቁሶችን የማደራጀትና የማዘጋጀት ኃላፊነት ነው።
በቤተ ጉራጌ ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ባለው ጊዜ ውስጥ በዓሉ በየቀኑ ልዩ ልዩ ባህላዊ ስያሜዎችና ሥርዓቶች ተሰጥተውት በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። በጋራ ሆነው ክትፎና መሰል ባህላዊ ምግቦችን እየተመገቡ በጭፈራና በፈንጠዝያ የመስቀልን በዓል ያከብራሉ።
የቀናቶቹን ስያሜና ባህላዊ ክዋኔ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሀገር ሽማግሌ ጐታ ኩየ እንደገለጹት፤ መስከረም 13 ቀን ‘ወሬት የኸና’ (እንቅልፍ ከልካዩ ቀን) ሲሆን በዚህ ቀን ሴቶች ለበዓሉ ዝግጅት ለማድረግ የሚጓጉበት ቀን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ቀን ለበዓሉ ለመመገቢያነት የሚያገለግሉ ባህላዊ ቁሳቁሶች ለዓመት ከተሰቀሉበት ቦታ ወርደው በጥንቃቄ ተጣጥበው ዝግጁ ይሆናሉ። ቀኑ ከአፈር በተዘጋጁ ቀለማት ግድግዳዎች የሚያሸበርቁበትና አዳዲስ ጅባዎች ተነጥፈው ለበዓሉ ዝግጁ የሚሆኑበት ቀን ነው።
መስከረም 14 ቀን ደግሞ ‘ደንጔሳት’ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ዕለቱ ልጆች ደመራ ደምረው ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን የሚያቀልጡበት ነው። ከደመራው በኋላም ሴቶች የጎመን ክትፎ በማዘጋጀት በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውክልና በተዘጋጀ ጣባ አድርገው ለምግብነት ያቀርባሉ። ባለትዳር የሆኑ አባላት በአንድ ጣባ የጎመን ክትፎው ተዘጋጅቶ ይሰጣቸዋል። ተምሳሌትነቱም የትዳር አጋሮች "አንድ አካል፣ አንድ አምሳል ናቸው" ተብሎ ስለሚታመን የሚፈፀም ነው።
ጉራጌዎች ‘ወኸምያ’ ብለው የሚጠሩት መስከረም 15 ዋናው የመስቀል በዓል የሚውልበት ቀን ነው። በዚህ ዕለት ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለየ በሁሉም የቤተ ጉራጌ አካባቢዎች የእርድ ቀን ነው። በሌሎች አካባቢዎች ዕለቱ መስከረም 17 ቀን ላይ እንደሚከበር ልብ ይሏል። በ 'ወኸምያ' ቀን የሚታረደው በሬም ሆነ ወይፈን በሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ ስለ ሀገር ሰላም እንዲሁም በዓሉ መልካም ነገር እንዲያመጣ ምርቃት ይወርዳል። የቤተሰቡ አባላትም በእያንዳንዱ ምርቃት መጨረሻ ላይ “ኬር ኬር ኬር ይሁን” (ሰላም ይሁን) በማለት ምርቃቱን ይቀበላሉ። በዚህ ባህላዊ የምርቃት ሥነ ሥርዓት አብዛኛውን ጊዜ እንዲመርቁ የሚጋበዙት በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ አረጋውያን ሲሆኑ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እኩል ተሳትፎ ይኖራቸዋል።
መስከረም 16 ቀን (‘ያባንዳ እሳት’ ወይም 'የጉርዝ ኧሳት') የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ዕለቱ አባቶች ደመራ ይዘው የሚወጡበት ነው። በዚህ ዕለት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ የሚያደርግበት የደመራ በዓል ይከወናል። በዕለቱ አባቶች የተለየ ክብር ተሰጥቷቸው የደመራ በዓሉን በምርቃት ያስጀምሩታል። ቀኑ ከባህላዊ ይልቅ መንፈሳዊ ይዘትን ተላብሶ ይከበራል። ጎረምሶችና ልጃገረዶች ደመራውን በመክበብ በተለያዩ ጭፈራዎች አካባቢውን ያደምቁታል። ከጭፈራው በኋላም ሁሉም ወደ ቤቱ በመመለስ በራሱ ጣባ የተዘጋጀለትን ክትፎ ይመገባል።
ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በአንድ አካባቢ የሚገኙ የቤተ ጉራጌ ነዋሪዎች ደመራው ወደተቃጠለበት ቦታ በመሄድ የአካባቢያቸውን የዕድር ዳኛ በመቀየር አዲስ የሚመርጡበትና ቃለ መሐላ የማስፈፀም ተግባር የሚያከናውኑበት ቀን የሚከበረው መስከረም 17 ቀን ሲሆን ይህም ‘ንቅባር’ ወይም 'የከሰል ማይ' በሚል ስያሜ ይጠራል። በዕለቱም ሁሉም የአካባቢው የቤተሰብ አባላት የተቃጠለውን የደመራ ከሰል እየዘለሉ በመጪው ዘመን መልካም ነገር እንዲገጥማቸው ይመኛሉ፤ ይማፀናሉም። ወጣቶች ንጋት ላይ ተቀጣጥለው የቀሩ ጉማጅ እንጨቶችን ተሽቀዳድመው በመውሰድ እርሻ ላይ ያቆማሉ፤ ይህም እርኩስ መናፍስትን ይከላከላል ተብሎ ይታመናል።
መስከረም 18 ቀን ‘የፊቃቆ ማይ’ ይባላል። በዚህ ቀን የአካባቢው ልጃገረዶች ሰፌድ ለመስራት የሚያገለግል ስንደዶዎችን ይሰበስባሉ። የስንደዶ ለቀማው በባህላዊ ዜማዎች ታጅቦ ይከናወናል።
ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 ያለው ጊዜ ደግሞ የዘመድ መጠየቂያ ወቅት ሲሆን ‘የጀወጀ’ ወይም ‘የጀመቸ’ ተብሎ ይጠራል። ለዓመት ተነፋፍቀው የቆዩ ቤተሰቦች ተገናኝተው ናፍቆታቸውን የሚገልፁበት፣ የባልና ሚስት እናትና አባት የሚጠየቁበት እንዲሁም ስጦታ የሚቀበሉበት ዕለት ነው። ሴት ልጆች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ፣ ባርኔጣ፣ ጭራ እና ሌሎች ስጦታዎችን ሲያቀርቡ፣ ባሎቻቸው ደግሞ የበግ ሙክት በመያዝ ይጠይቋቸዋል። ስጦታው የቀረበላቸው እናትና አባቶችም የልጆቻቸውን ባሎችና ሚስቶች በየተራ ይመርቋቸዋል።
የጉራጌ ጋብቻ በብዛት የሚከወነው በዚሁ በመስቀል ሰሞን በመሆኑ፣ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ያለው ጊዜ በቤተ ጉራጌ ወጣቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው። በዚህ ጊዜ በተለያዩ የገበያ ቦታዎችና አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን ያሳያሉ፤ እግረ መንገዳቸውንም ለትዳር የምትሆናቸውን ጉብል መልከት መልከት ያደርጋሉ። የወጣቶቹ ባህላዊ ጨዋታ “አዳብና” በሚል ስያሜ የሚታወቅ ሲሆን፣ በንግድና በተለያዩ ምክንያቶች ቆይተው ስለመጡባቸው ቦታዎች ተገናኝተው የሚያወጉበትም ነው::