በሐረሪ ክልል ለተፈጥሮ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ለተፈጥሮ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል
ሀረር፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ለሚያጋጥሙ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር ገለጹ።
በአየር ንብረት መለዋወጥ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤልኒኖ ክስተት ጋር የተያያዘ ችግር ስለመኖሩ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሰሞኑን አመላክቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዘንድሮው የበጋ ወቅት በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ይጠበቃል ብሏል፡፡
በአንጻሩ በመካከለኛውና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ ያልተጠበቀ ዝናብ ሊኖር ይችላል ሲልም አሳውቋል።
በመሆኑም ለሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ በሐረሪ ክልል ያለውን ዝግጁነት በተመለከተ ኢዜአ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አነጋግሯል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር፤ በማብራሪያቸው በክልሉ በአየር ንብረት ለውጥ ሊያጋጥም የሚችልን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ስለመደረጉ ገልጸዋል።
በራስ አቅም የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት ስራ ሲከናወን መቆየቱን በማስታወስ ለሚያጋጥሙ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በክልሉ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ቀደም ብሎ በመለየት የመስኖና የከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም የማልማትና የምርት አማራጮችን የማስፋት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም በቤተሰብ ደረጃ ጭምር በምግብ ራስን የመቻል ስኬት መኖሩን አንስተው የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም ኢንሸቲቮች መሰረታዊ ለውጥ ያመጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምርትና ምርታማነት አቅምን በማሳደግ ከተረጅነት ለመላቀቅ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል።
በዚህም በተለይ የዝናብ እጥረት ሲያጋጥም ክስተቱን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው ፈጥነው የሚደርሱ ምርጥ ዘሮች በመለየት የውሃ እጥረትን የሚቋቋሙ ሰብሎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የምርት ክምችት የማድረግና ድጋፍ የመስጠት እንዲሁም የከብት መኖ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ላይም እየጣለ የሚገኘውን ዝናብ በማጠራቀም አርሶ አደሩ ባለው መሬት እንዲያለማ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይም የአየር ንብረትና ሁኔታ መረጃን ለአርሶ አደሩ የማድረስና የመስኖና የከርሰ ምድር ውሃ ሃብትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን የበለጠ የማሳደግ ስራዎች እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል።
የሐረሪ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤልያስ መሀመድ በበኩላቸው የኤልኒኖ ክስተት በአንዳንድ አካባቢዎች ጉዳት እንዳያስከትልና አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲቻል የአደጋ መከላከልና ፈጣን ምላሽ ሰጪ ምክር ቤት መቋቋሙን ተናግረዋል።
በዚህም ችግሩ የታየባቸውን አካባቢዎች የመለየትና ምርጥ ዘር በማከፋፈል ወደ ምርት እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተለይም የምግብ እጥረት እንዳይከሰት በራስ አቅም መቋቋም የሚያስችል የምርት ክምችት የማድረግ ስራም መከናወኑን ገልጸዋል።