ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ በቀጣናው ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን ወሳኝ ነው 

ጅማ ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ከሚያስገኝላት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ባሻገር በቀጣናው አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈንና የጋራ ልማትን ለማፋጠን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል ያግዛታል ሲሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ የራሷን የኢኮኖሚ ጫና ከመቀነሱም በላይ፣ የቀጣናውን የባሕር ደህንነት በመጠበቅ የጋራ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ረገድ የምታበረክተውን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ በዳሳ ፍራጃ (ዶ/ር)  እንደተናገሩት፣ የባህር በር አለመኖር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው የጸጥታ እንቅስቃሴዎች ላይም ተፅዕኖ በማሳደር ለተለያዩ ፈተናዎች ዳርጓታል።


 

የባህር በር ማግኘቷም ሀገሪቷ በቀይ ባህር አካባቢ በንቃት እንድትሳተፍና በአካባቢው የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ላይ የበለጠ ሚና እንድትጫወት እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ ታጣቂዎችና የባህር ላይ ወንበዴዎች ያሳደሩትን ተፅዕኖ በማንሳት፣ በአካባቢው የሚፈጠሩ የጸጥታ ስጋቶች ከቀጣናው አልፈው ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል አብራርተዋል።

ቀድሞ የነበራትንና በሴራ ያጣችውን የባህር በር ማግኘቷ ታዲያ ኢትዮጵያ የጸጥታ ስጋቶችን በመመከት ያካበተችውን ልምድ በመጠቀም በቀጣናው የሰላምና የጸጥታ ጥረቶች ውስጥ የሚኖራትን ሚና ለማጠናከር ያስችላታል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የባህር በር ማግኘቷ በአካባቢው የልማት ትስስርን ለማጠናከርና ከቀይ ባህር አዋሳኝ ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፋት ዕድል ይፈጥራል።

በመሆኑም የዲፕሎማሲ ጥረቷን ከማጠናከር ባለፈ የአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መርህን በመከተል ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ መስራት እንዳለባትም ጠቁመዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ምህንድስና መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ማሙዬ ቡሴር፤ የባህር በር ጉዳይ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥቅም ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ያነሳሉ።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ማሙዬ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ጠንካራ የባህር ኃይል የነበራት ከመሆኑም በላይ የቀይ ባህርን አገልግሎት በቅርበት ትጠቀም ነበር።

የአሁኑ የባህር በር ጥያቄንም የኢትዮጵያ ብቻ አገራዊ ፍላጎት አድርጎ ከመመልከት ይልቅ፣ ከአጎራባች አገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ትውልዱ በጋራ በመቆም መስራት እንደሚገባው ምሁራኑ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም