ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የወረርሽኝ ቀድሞ ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅሟን እያጠናከረች ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተከስተው ከነበሩ ወረርሽኞች ትምህርት በመውሰድ የወረርሽኝ ዝግጁነት፣ ቀድሞ ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅሟን እያጠናከረች መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢንስቲትዩቱ የወረርሽኝ ስጋትን ቀድሞ በመለየትና በመከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቴክኖሎጂ ራሱን እያበቃ መሆኑን ጠቁመው፤ የሀገር ውስጥ የምርመራ አቅምን ማሳደጉንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 እና በማርበርግ ወረርሽኞች ወቅት ካጋጠሟት ፈተናዎች በመማር የወረርሽኝ ዝግጁነት፣ ቀድሞ ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅሟን እያጠናከረች መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ወረርሽኞች ከችግር በኋላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ቀድሞ ዝግጁ የሆነ ሥርዓት መገንባት ያለውን ጠቀሜታ ያሳዩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በላቦራቶሪ አቅም፣ በአሰራር ሥርዓትና በወረርሽኝ ማስተባበሪያ መዋቅሮች ላይ መዋዕለ-ንዋይ መፍሰሱን ገልጸዋል።

በዚህም በክልልና በዞን ደረጃ 24 የሚደርሱ የድንገተኛ አደጋ ኦፕሬሽን ማዕከላት ተስፋፍተው ከብሔራዊ ማዕከል ጋር ተሳስረው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የአቅም ግንባታ ስራው ውጤታማነት በማርበርግ ወረርሽኝ ወቅት ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰው፣ በዚህም በአጭር ጊዜ ወረርሽኙን መቆጣጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የድንገተኛ ምላሽ ቡድን በዓለም ጤና ድርጅት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ሲቪል ቡድን ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ መመደቡ የአቅም ግንባታ ስራው ውጤት አንዱ መሳያ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ኢንስቲትዩቱ ቀደም ሲል ምርመራዎችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ውጤት ለማግኘት ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት ይፈጅበት እንደነበር አውስተው ከዚህ በመነሳት የሀገር ውስጥ የምርመራ አቅምን ማሳደጉንም አረጋግጠዋል።

ይህንን አቅም ወደ ክልሎች በማስፋፋት የምርመራ ሥራውን ወደ ማህበረሰቡ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የመጓጓዣ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የምርመራ ውጤትን በፍጥነት ለማሳወቅ ይረዳል ብለዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ የወረርሽኝ ምላሽን ብቻ ሳይሆን ቀድሞ መከላከልን ለማጠናከር የእያንዳንዱን ወረዳ የዓመት የጤና ስጋት የመመርመር እና የመለየት ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከአሁንና ከቀደምት ዓመታት መረጃ በመነሳት ቀጣይ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን ለመተንበይ ሳይንሳዊ የሞዴሊንግና የትንበያ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም አክለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የዲጂታል መረጃ ሥርዓቱን ለማጠናከር ባከናወናቸው ተግባራት ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ያለውን የመረጃ ፍሰት በአውቶሜሽን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማስገባቱን አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረት የሚሰበሰበው መረጃ ለውሳኔ አሰጣጥና ለወደፊት ትንበያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ነው ዶክተር መልካሙ የተናገሩት።

በቀጣይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በማስተዋወቅ የቅኝትና የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሥራውን ለማጠናከር ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም የላቦራቶሪ፣ የዲጂታል መረጃ፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ፣ የሳይንሳዊ ትንበያና የፈጣን ምላሽ አሰጣጥ አቅሞችን በማጠናከር የወረርሽኝ ስጋቶችን ቀድሞ መለየትና መቆጣጠር የትኩረት አቅጣጫው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም