ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ትልቅ አቅም እየሆነ ነው 

ሀዋሳ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን  ተፅዕኖ  በመቋቋም  ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ትልቅ አቅም እየሆነ መምጣቱን  በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የዘርፉ ተመራማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ  የሚያስከትለውን ተፅዕኖ  በመቋቋም ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያስቻለ ነው።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ለመንከባከብ የተሰጠው ሀገራዊ ትኩረት ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማፋጠን ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አመልክተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ  መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፀጋዬ በቀለ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ንቅናቄን በመፍጠር መላውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የተከናወነው ተግባር በዘርፉ አስደናቂ ውጤት አስመዝግቧል። 


በሀገር አቀፍ ደረጃ  ችግኝን የመትከልና የመንከባከብ ባህል እያደገ በመምጣቱ ዘርፍን የተሻለ ውጤት እንዲታይበት አድርጓል ብለዋል።

ይህም ተፈጥሮን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን  ችግር በመቋቋም የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  የጎላ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ፕሮፌሰር ፀጋዬ ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ የመሬት ለምነትና የውሃ አቅም በማሻሻል የግብርና ምርትና ምርታማነት ለመጨመር  ማስቻሉንም ተናግረዋል።

ንብ ማነብን  ጨምሮ አዳዲስ የስራ ዘርፎች በስፋት እንዲፈጠሩ በማድረግ የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

የኮሌጁ ዲን ተሻለ ወልደአማኑኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት አመርቂ ውጤቶች እያስገኘ  ነው።


 

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታከናውነው  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ትልቅ አርአያ መሆኑን ተናግረዋል።

የስነ-ምህዳር እና ብዝሃ ህይወት በዘላቂነት እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ መርሃ ግብሩ  የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ኮሌጁ ከሀገሪቱ መልክአ ምድርና ስነምህዳር ጋር የሚስማሙ ችግኞችን  በምርምር በማውጣት እንዲሁም  በማፍላትና  በማሰራጨት መርሃ ግብሩን በመደገፍ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት እየተወጣ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

ኮሌጁ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ልምድ ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲስፋፋ በጥናት የተደገፉ ሰነዶች በማዘጋጀት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል  ተሻለ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም