ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ብልጽግናን ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ብልጽግናን ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በውሃ ሀብት የጋራ ቀጣናዊ ብልጽግና ልማት እውን ማድረግ እንደሚቻል ያረጋገጠ ታላቅ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።
ፕሬዝዳንቱ ማምሻውን በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በንግድ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በኩል በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስርና ትብብርን ለማጠናከር በትጋት እየሠራች መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
አንዳንድ የውጭ አካላት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አለመረጋጋት ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን አንስተው፤ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ብለዋል።
ከኢነርጂ ጋር በተያያዘ፣ ኢትዮጵያ ከ60,000 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ማመንጨት አቅም እንዳላት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ ተጨማሪ 13,000 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ማቀዷን ጠቁመዋል።
ይህም የምሥራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ገበያና ከዚያም አልፎ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል አስታውቀዋል።
በዚህ ረገድም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሀብት የጋራ ቀጣናዊ ብልጽግና ዕድገትና ልማት መፍጠር እንደሚቻል ያረጋገጠ ታላቅ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት ነውም ብለዋል።
በሌላ በኩል በዲጂታል አብዮትና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን አፍሪካ የምታነሳው ወሳኝ ጥያቄ የቴክኖሎጂው ዘመን ዓለም አቀፍ አለመመጣጠንን የሚያባብስ ወይስ የጋራ እድገት ማፋጠኛ ነው? የሚለውን ጥያቄ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል።
ዓለም አቀፉ የደቡብ ክፍለ ዓለም የቴክኖሎጂ አብዮቱን በባለቤትነት መምራት እንጂ ተመልካች መሆን የለበትም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" መርሃ ግብር እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ አህጉሪቱ ለቀጣዩ ጊዜ ዝግጁ መሆኗን ማሳያ ናቸው ብለዋል።
ከአካባቢ ጥበቃ እና ከተፈጥሮ ሀብት አንፃርም፤ ከስምንት ዓመታት በፊት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስከ አሁን 56 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ፕሬዝዳንቱ አስታውሰዋል።
መርሃ ግብሩ የደን ሽፋን ከማስፋቱም በላይ የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን ወደ ነበረበት እየመለሰ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ይህም በዓመት 9 ቢሊዮን ቶን ካርቦን የማመቅ አቅም እንደሚኖረው ይጠበቃል ብለዋል።