አፍሪካውያን በተመድ ፍትሃዊ ውክልና መነፈጋቸው በአስቸኳይ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን በተመድ ፍትሃዊ ውክልና መነፈጋቸው በአስቸኳይ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን አፍሪካውያን በተመድ ፍትሃዊ ውክልና መነፈጋቸው በአስቸኳይ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
ተመድ የዓለምን ነባራዊ እውነታ ያገነዘበ መሰረታዊ ሪፎርም ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።
81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ማምሻውን በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ በንግግራቸው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሁኑ ሰዓት ዓለም ላይ ፈታኝ ሁኔታዎችን በተሻለ አቅም መፍታት እንዲችል መሰረታዊ የሆነ ሪፎርም እንዲያደርግ አጥብቃ ታሳስባለች ብለዋል።
ተመድ በእኩልነት እና ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የዓለምን ነባራዊ እውነት ባገነዘበ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተግላ መቆየቷን አውስተው የፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ሪፎርም ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
"እውነተኛ የፖለቲካ ፍላጎት ካለ፣ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን አፍሪካውያን እኩል ውክልና የማግኘት መብት ለዘመናት መነፈጋቸውን እንዴት የዓለም ህሊና ሊቀበለው ይችላል?" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል።
ይህ የትውልዱ የእውነት እና የሞራል ጥያቄ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቱ የባለብዙ ወገን ትብብርን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፤ የጋራ ጸጥታ ምሰሶዎች ሙሉ በሙሉ ከመፍረሳቸው በፊት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ግጭቶችን ለመከላከል አበክሮ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለብዙ ወገን ትብብር እንደ ቀላል የዲፕሎማሲያዊ መሳሪያ አይደለም፤ ይልቁንም ዓለም አቀፍ የኃይል ፖለቲካን ለመቋቋም የሚያስችል እና በሉዓላዊ እኩልነት ላይ የተመሰረተ ህያው ጋሻችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ፣ ፍትሕ እንዲሰፍን እና የነፃ ሕዝቦች ጽኑ አብሮነት እንዲከበር ባላት ታሪካዊ ቁርጠኝነት ጸንታ እንደምትቀጥል ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።