ኢትዮጵያ ኮፕ 32 ሁሉን አካታች እና መፍትሔ አምጪ እንዲሆን በቁርጠኝነት ትሠራለች – ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ኮፕ 32 ሁሉን አካታች እና መፍትሔ አምጪ እንዲሆን በቁርጠኝነት ትሠራለች – ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ሁሉን አካታች እና መፍትሔ አምጪ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደምትሠራ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።
“መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሠራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መፍጠር” የጠቅላላ ጉባኤው መሪ ሐሳብ ነው።
በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ፕሬዝዳንቱ ማምሻውን በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንደምታዘጋጅ ገልጸዋል።
ጉባኤው የግሉን ዘርፍ እና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ሁሉን አካታች እና መፍትሔ አምጪ እንዲሆን ኢትዮጵያ አበክራ እንደምትሠራ ተናግረዋል።
ሁሉም የዓለም መሪዎች በኮፕ ጉባኤው ላይ እንዲሳተፉና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።