“ቅጠል ተራ” ወደ “መርካቶ የበጎነት መኖሪያ መንደር” ተቀይሯል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
“ቅጠል ተራ” ወደ “መርካቶ የበጎነት መኖሪያ መንደር” ተቀይሯል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13 /2019 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ቅጠል ተራ” በሚባለው አካባቢ በአራት ወራት ውስጥ የገነባቸውን 960 ቤቶች ዛሬ ለልማት ተነሺዎች አስረክቧል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ “ቅጠል ተራ”ን ለዜጎች ክብር የሚመጥን ንጹሕና አረንጓዴ የመኖሪያ ስፍራ መቀየር መቻሉን ገልጸዋል።
የቀድሞው “ቅጠል ተራ” ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ፣ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን፣ ቆሻሻ፣ የተፋፈገና የተጨናነቀ በመሆኑ በእሳት አደጋ የነዋሪዎችን ሕይወት ጭምር አጥተናል ብለዋል።
አሁን ግን በስፍራው ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ መገንባቱን ጠቁመው፣ ዘጠኝ ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንፃዎች ተገንብተው አካባቢው ወደ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ መቀየሩን ገልጸዋል።
“መርካቶ የበጎነት መኖሪያ መንደር” በ11 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነቡ ዘጠኝ G+8 ብሎኮች የተደራጀ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 960 ቤቶችን ያካትታል።
በመንደሩ 371 የንግድ ሱቆች፣ የሕጻናት መጫወቻ ስፍራ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያና የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ መኖሩን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ዘጠኙም ብሎኮች የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፣ ሊፍት፣ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች የተሟሉላቸው ሲሆን፣ በዘመናዊ መልክ መገንባታቸውንም ጠቁመዋል።
“መርካቶ የበጎነት መኖሪያ መንደር” በመርካቶ ዙሪያ “ተራ” የሚል ቅጥያ ያላቸውን እንደ ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራና ቦንብ ተራ ያሉ ጎስቋላ ሰፈሮችን ወደ ውብና ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎች የሚቀይር ሰው ተኮር ልማት ማሳያ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
“ያለ እረፍት 24/7 በመሥራት፣ የተወሳሰበ ችግር ያለባቸውን መሰል አካባቢዎች የሰው ልጅ ክብርን ወደሚመጥኑ ምቹ የመኖሪያ መንደሮች በመቀየር ነዋሪዎች አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ በማድረግ ቃል በተግባር መተርጎማችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።