ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቅጠል ተራን ወደ ንፁህ አረንጓዴ ለዜጎች ክብር የሚመጥን መኖሪያ ስፍራ መቀየር መቻሉን አመልክተዋል።
በቅጠል ተራ 960 ቤቶች በአራት ወር ውስጥ ተገንብቶ ከቦታው ላይ ለተነሱ ነዋሪዎች መተላለፉን ተናግረዋል።
ከንቲባዋ አያይዘውም፣ ቅጠል ተራ ለመኖር እጅግ ምቹ ያልነበረ፤ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን፤ እጅግ የቆሸሸ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ በመሆኑ የሰው ህይወትም በአስከፊ ሁኔታ በእሳት አደጋ ያጣንበት አካባቢ ነበር ብለዋል።
ዛሬ ግን እጅግ ያማሩ፥ ዘመናዊና ሁሉንም ነገር የተሟሉላቸው ባለ 9 ወለል የሆኑ ብዛታቸው 9 ህንጻዎች 960 ቤቶች ተገንብተው ወደ ምቹ መኖሪያ አካባቢ ተቀይሯል ሲሉ ገልጸዋል።
በመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር በ11,000 ካሬ ሜትር ላይ የተገነቡ G+8 የሆኑ ዘጠኝ (9) ብሎኮች በአጠቃላይ 960 ቤቶች ያሉት ሲሆኑ፣ ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች በውስጡም የህጻናት የመጫወቻ ስፍራ፣ የስፓርት ማዘውተሪያ (የኳስ ሜዳ፣ ቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ፥ የሰውነት ማጎልመሻ ቦታዎች) ፥ ለነዋሪዎች የመኪና ማቆምያ ፓርኪንግ፥ ለኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፥ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ፥ዘጠኙም ብሎኮች ላይ የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፥ ሊፍት፥ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች በዘመናዊ መልክ ተሟልተው ተገንብተዋል ።
ይህ በመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር የሰው ህይወትን የሚቀይር ፥ መርካቶ አካባቢን “ተራ” በሚል ስያሜ የተሰጣቸው (ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ፣ ቦንብ ተራ … ወዘተ) ጎስቋላ አካባቢዎችን ወደ ውብ አካባቢ የመለወጥ ጉልህ ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት ከንቲባዋ።
ቃል በተግባር ማለት ይህ ነው፥ እንደዚህ ዓይነት የተወሳሰበ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ለሰው ልጆች የሚመጥኑ፥ ነዋሪዎች የክብር ኑሮ እንዲኖሩ፥ ህይወታቸውን የሚቀይሩ ተግባራትን ያለ እረፍት ሰርቶ በመፈፀም ነዋሪዎች አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ማድረግ ነው ብለዋል ከንቲባዋ።
የስራዎቻችንን ማዕከል ሁሉ ሰው ተኮር አድርገን፥ ከተማችን ውብ ፅዱ፥ ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አክለዋል።
ካላችሁ አካፍላችሁ ከከተማ አስተዳደራችን ጎን በመሆን የበጎ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ፥ ዛሬም በቅጠል ተራ የበጎነት መንደር እንድንቀይር ያገዛችሁን በተለይ ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ፥ በግንባታው የተሳተፋችሁ ሁሉ በነዋሪዎች ስም ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ቅጠል ተራ ወደ “መርካቶ የበጎነት መንደር “ ተቀይፘል ! በማለት ከንቲባዋ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።