ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ባህር ዳር ፤ መስከረም 13/2019 ( ኢዜአ) ፦ በባህር ዳር ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት የማሳደግና አልሚዎችን በመሳብ የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በወቅቱ እንደገለጹት የከተማውን አምራች ኢንዲስትሪዎች ምርታማነት የማሳደግና ኢንቨስትመንትን በመሳብ የተገኙ ውጤቶች ይጠናከራሉ።


 

ለዚህም የግብርናና የኢንዱስትሪውን የግብአት ትስስር በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን በማጎልበት በኩል ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።

ይህም የፋብሪካ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለውጭና ለሀገር ውስጥ  ገበያ በማቅረብ  ምንዛሬ ከማስገኘት ባለፈ ተኪ ምርቶችን  ማምረት መቻሉን  ገልፀዋል።

ከተማውን ከቱሪዝም ማእከልነት በተጨማሪም በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፋ እድገት እንዲፋጠን አግዟል ብልዋል።


 

በተለይም ኢንዱስትሪዎች ያጋጥማቸው የነበሩ የመሰረተ ልማትና መሰል ችግሮችን በተቀናጀ አመራር በመፍታት ወደ ተሟላ ምርታማነት እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

አንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ተመርተው ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች የአካባቢውን የገበያ ዋጋ እና የኑሮ ውድነት በማረጋጋት አይተኬ ሚና እየተወጡ ይገኛል ብለዋል።

በመድረኩ የከተማው አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በየዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም