ከቱሪዝም: 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
ከቱሪዝም: 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ጎብኚዎችን በማስተናገድ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ ጊዜ "ዲጂታል አጀንዳ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለቱሪዝም አዲስ ቅኝት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን የቱሪዝም ቀን እና ያለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፍ አፈፃፀምና የቀጣይ ዕቅድ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በመግለጫቸው፤ የቱሪዝም ዘርፍ በፍጥነት በማደግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጉልህ እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ባህሎች እንዲተዋወቁ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ገንቢ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት አዳዲስ መዳረሻዎችን በመገንባት፣ ነባሮችን በማደስ በተጠናቀቀው የ 2018 በጀት ዓመት ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ጎብኝዎች 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
በኮንፍረንስ ቱሪዝም 120 ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ታቅዶ 220 በማዘጋጅት የኢትዮጵያን ገጽታ መገንባት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ አያይዘውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ39ኛው የቱሪዝም ቀን ከመስከረም 14 እስከ 17 ቀን 2019 ዓ.ም ይከበራል ብለዋል።
የቱሪዝም ቀን ክብረ በዓል የቱሪዝም ዘርፉን መፃኢ ዕድሎች የሚያስተዋውቅ ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንዳለው በማንሳት፤ በአዳዲስና ነባር የቱሪስት መዳረሻዎች በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ገልጸዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸው፤ ይህንን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፤ ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ የቱሪስት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዲጂታል የቱሪስት የመረጃ ማዕከል ሥራ አስጀምረዋል።
የዲጂታል ማዕከሉ ለጎብኝዎች የተደራጀ መረጃ የሚሰጥ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን በቀላሉ የሚያስተዋውቅ መሆኑን ገልጸዋል።