ቀጥታ፡

ኢሬቻ የሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና የብዝኃ-ባሕል መድረክ ነው - የታሪክ ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና ሥርዓት ከመሆኑ ባሻገር የሌሎች ብሔሮች ብዝኃ-ባህልና ወንድማማችነት የሚንፀባረቅበት መድረክ መሆኑን የታሪክ ተመራማሪዎች አስረዱ።

በኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የዘርፉ ምሁራን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢሬቻ ማለት የኦሮሞ ሕዝብ በፀደይና በበልግ ወራት ወደ ወንዝና ተራራ በመውጣት ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ከመሆኑ ባሻገር ብዝኃ-ባህልና ወንድማማችነት የሚንፀባረቅበት መድረክ ነው ብለዋል።

በኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ግርማ ነመራ እንዳመለከቱት፤ በዓሉ የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የሕዳሴ ምልክት ከመሆኑም በላይ የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ሥርዓቱን ጠብቆ ያቆየው ነው ብለዋል።

ተመራማሪው አክለውም ኢሬቻ በርካታ ዓይነቶች ያሉት ሲሆን፤ እነሱም፦ ኢሬቻ ቀዬ(የአካባቢ)፣ ኢሬቻ ቱሉ (የተራራ ኢሬቻ እና ኢሬቻ መልካ (የወንዝና ሃይቆች ዳርቻ ኢሬቻ) መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የማንነቱ መገለጫ ምልክት ከመሆን ባሻገር ሌሎችም ህዝቦች ከውጭ ሀገርና ከሀገር ውስጥ ተገኝተው ባህላቸውን የሚያደምቁበት መድረክ ሆኗል ብለዋል።

በዓሉ ፈጣሪን ከማመስገን ባለፈ የኦሮሞ ሕዝብ ከየአቅጣጫው ተሰብስቦ አንድነቱ የሚታይበት፣ ባህልና እሴት የሚማማሩበት ስፍራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢሬቻ የእውነት ስፍራና ሰዎች አብሮነታቸውን ለዓለም የሚያሳዩበት፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የሰላምና የወንድማማችነት መድረክ እንደሆነም አብራርተዋል።

በኢንስቲትዩቱ የስነ-ጥበብ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ማሞ ሶቦቅሳ በበኩላቸው ኢሬቻ ከኦሮሞ ባህላዊ ክዋኔዎች አንዱና ትልቁ መሆኑን ገልጸው፤ ሕዝቡም ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት እሴት ነው ብለዋል።

በተለይም ኢሬቻ መልካ ከባዱ የክረምት ወራት አልፎ ለፀደይ ብርሃን ስላበቃቸው ሰዎች ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት ሥርዓት መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህ የምስጋና ሥርዓት የራሱ የሆነ የአካሄድ ሕግና እሴት ያለው ሲሆን፤ ልጃገረዶች (ቀሬ) ከፊት በመሆን፣ እናቶች ይከተላሉ፣ በመቀጠል አባቶች፣ እንዲሁም ወጣቶችና ፎሌዎች እየዘመሩና እየጨፈሩ የሚከተሉበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ወደ ኢሬቻ በሚኬድበት ጊዜ ከሚዘመሩት ዘፈኖች መካከል በዋናነት "መሬ ሆ" የሚለው የሚሰማ ሲሆን፤ ይህም "ዓመት ዓመት በሰላም ያደረስከን አምላክ ምስጋና ይግባህ" የሚል ትርጉም እንዳለውና "መሬሆ" ማለት ዞሮ መጣ ማለት እንደሆነ አቶ ማሞ አስረድተዋል።

ኢሬቻን አክብረው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ደግሞ እማኝነታቸውን ለአምላክ እየሰጡ "ገቢሰዮ" እያሉ እየዘመሩ እንደሚመለሱ አብራርተዋል።

በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና ሥርዓት ከመሆኑ ባሻገር የሌሎች ብሔሮች ብዝኃ-ባህልና ወንድማማችነት የሚንፀባረቅበት፣ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰባሰበው ህዝብ ደምቆ የሚታይበት መድረክ መሆኑንም አስረድተዋል።

አባቶችና እናቶች ከፍተኛ ሥርዓትና ባህላዊ እሴት ያለውን ይህን ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ እንዳስተላለፉት ሁሉ፣ እኛም ባህላችንን አጠናክረን ለተተኪው ትውልድ ማውረስ አለብን ሲሉም ተመራማሪዎቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም