ቀጥታ፡

አዲስ መንግሥት፣ የላቀ ድል!

ኢትዮጵያውያን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በድምጻቸው ይሁንታ የሰጡት ፓርቲ መንግሥት የሚመሰርትበት ቀን ይፋ ሆኗል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ዛሬ ይፋ እንዳደረጉት፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀመር በተደነገገው መሠረት፣ የመንግሥት ምስረታውና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይከናወናል።

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መንበር ያገኘው የፖለቲካ ፓርቲ የፌደራሉን ሕግ አስፈጻሚ አካል የሚያደራጅ ሲሆን፣ በሕዝብ የተመረጠው አዲሱ ሕግ አስፈጻሚ አካል በዕለቱ በይፋ ኃላፊነት ይረከባል።

ይህም የፖለቲካ ሕጋዊነትን በጽኑ መሰረት ላይ የመገንባት እና ተቋማዊ ሽግግርን በተሳካ ሁኔታ የማረጋገጥ ሀገራዊ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያ ወደ እዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ለመሸጋገር በርካታ መንገዶችን ተጉዛለች።

ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች፤ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 10 ሺህ 438 ዕጩዎች የተሳተፉበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ደግሞ በዚህ ረገድ በጉልህ የሚጠቀስና የኢትዮጵያ የማድረግ አቅም የተገለጸበት ሀገራዊ ሁነት ነው።

ምርጫው በትልቅነቱ ብቻ ሳይሆን በትርጉሙም ኢትዮጵያ በቀጣናው ታላቅ ሀገር መሆኗን በተግባር ያሳየ ነው። ውስብስብ ሂደት የሚጠይቀውን ይህንን ምርጫ ነጻ፣ አሳታፊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን አድርጋ በውጤታማነት ያጠናቀቀችበት ሂደትም በበርካቶች አድናቆት የተቸረው ስኬት ነው።

ከሀገራዊ ድንበር ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የምትጫወተው የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን፣ በሀገሪቱ የተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የቀጣናውን የፖለቲካ መረጋጋት የሚያጎለብት ታላቅ አወንታዊ ምልክት ነው።

አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማደረግ አዲስ መንግሥት በመመስራት ወደ ሥራ ለመግባት ቀን ቆርጣ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የሚመሰረተው አዲስ መንግሥት ከ130 ሚሊዮን በላይ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አዲስ ማህበራዊ ውል (Social Contract) የሚፈጸምበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

አዲስ መንግሥት መመሥረቱ ደግሞ የታቀዱ ታላላቅ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ መዋቅራዊ ለውጦችን እና የልማት ፕሮጀክቶችን በሙሉ ራስ መተማመን ለማስፈጸም ተጨማሪ ዕድልና ጉልበት ይፈጥራል።

ለ2019 በጀት ዓመት የሚውል 2 ነጥብ 34 ትሪሊዮን ብር የፌዴራል መንግሥት በጀት በይፋ መጽደቁ ይታወሳል። ይህ በጀት በሀገር ውስጥ የሚመነጭ ኢኮኖሚን በማጠናከርና የውጭ የንግድ ብድርን በመቀነስ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (GDP) ዕድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሠረት እንደሚጥልም ታምኖበታል።

እየተተገበሩ ያሉ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች፣ የዋጋ ንረትን ባለ አንድ አሃዝ ለማድረስ የተጀመረው ጥረት ውጤት እያደረጉ ሲሆን ማሻሻያዎቹ እንደሚቀጥሉም ይጠበቃል።

ለሴቶችና ለገጠር ማኅበረሰብ የሚደረጉ የሥራ ዕድል ፈጠራና የኑሮ ማሻሻያ ስራዎች፤ የቤት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት እና የኃይልና የመስኖ ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቅ ሥራዎችም በአዲሱ መንግሥት ከሚጠበቁ ስራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም ዜጎች ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በቢሮክራሲ የሚፈጠሩ እንግልቶችን ማስወገድና ጊዜን ወደ ምርታማነት መቀየር የአዲሱ ዘመን መለያ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያገኘቻቸውን ስኬቶች የማስቀጠል እንዲሁም የኮፕ 32 የዝግጅት ሂደትም ሌላኛው የትኩረት መስክ ይሆናል።

ኮፕ 32 የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬቷን የሚያሳይ ሲሆን፤ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶቿ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም