በቀለማት ያሸበረቀው አስደናቂው የቱሪዝም መስህብ ስፍራ - ኢዜአ አማርኛ
በቀለማት ያሸበረቀው አስደናቂው የቱሪዝም መስህብ ስፍራ
ኢትዮጵያ ከዳሎል እስከ ራስ ዳሽን አስደናቂ መልክዓ ምድር የሚገኝባት ድንቅ ሀገር ነች። የሰው ዘር እና የቡና መገኛ በመሆንም ዓለም በልዩነት የሚያነሳት፣ የ13 ወራት የብርሃን ጮራ የሚፈነጥቅባት፣ ለኑሮ እና ለግብርና ልማት በእጅጉ ተስማሚ የሆነ መሬትና ምቹ አየር ንብረት የታደለች ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ሉሲ እና ሌሎችም ቅሪተ አካሎች ተገኝተው ጥናትና ምርምር ተደርጎባቸው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ምድር መሆኗን ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ተችሏል። በዚህም በሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ የምርምር ሂደት የዓለም ሳይንቲስቶችን ቀልብ የገዛ ሆኗል። ለሚሊዮን ዓመታት የቆዩ አጥንቶችና የጥንት የድንጋይ መሣሪያዎች ሳይበላሹ ቆየተው የተገኙበትም ነው። በዚህም ዓለም አቀፍ አርኪዮሎጂስቶችን፣ የታሪክ አዋቂዎችን እና የተመራማሪዎችን ልዩ ትኩረት ያገኘ ስፍራ ነው።
ኢትዮጵያ ቡናንም አብቅላ ለዓለም በማበርከት የቡና መገኛ ተብላ ስሟ በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። የቡና ወዳጅ የሆኑ ሁሉ የኢትዮጵያን ቡና በማጣጣም የጥራት ልኬትና የልዩ ጣእም ምልክት አድርገውም ይወስዱታል። የቡና ስነ-ሥርዓቷም የሀገሪቱ እሴትና የቱሪዝም መገለጫ መሆኑ ይታወቃል።
በአፋር ክልል የሚገኘው በምድር ላይ ካሉ እጅግ ሞቃታማ እና ድንቅ ስፍራዎች አንዱ የሆነው ዳሎል፣ በቀለማት ያሸበረቁ የሰልፈር ምንጮች፣ የጨው በረሃዎች እና በእንፋሎት የሚንቀለቀሉ መልክዓ ምድሮቹ አስደናቂ ስሜትን ይፈጥራሉ። ኤርታሌም በዓለም ላይ ከሚገኙ የማያቋርጥ የላቫ ሐይቅ ካላቸው ስፍራዎች አንዱ ሲሆን በምሽት ላይ የሚታየው የእሳት ወጀብ ለአድቬንቸር ቱሪዝም አፍቃሪዎች ትክክለኛ መዳረሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በአፋር ምድረ በዳ ላይ የሚንተከተከው የእሳት ወላፈን መፍለቂያው “ኤርታሌ” ከዓለም አስደናቂ ስፍራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። ኤርታሌ "የሚያጨስ ተራራ" የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በላዩ ላይ ሁልጊዜ የሚበራና የሚፈላ የማግማ (ላቫ) ሐይቅ አለው። በአካባቢው ብድግ ቁጭ ሲል የሚታየው የእሳት ርችት አስደናቂ ትእይንት መሆኑን ጎብኝዎች ይመሰክሩለታል።
ከባሕር ጠለል በታች እስከ 120 ሜትር (390 ጫማ) የሚገኘው የዳሉል ዝቅተኛ ስፍራ በምድር ላይ ከሚገኙ እጅግ ሞቃታማ አካባቢዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የዳሉል ዝቅተኛ ስፍራ በሚያስደንቅ የጂኦሎጂካል ሂደቶች የተፈጠረ ነው። በምድር ውስጥ ያሉ ማዕድናት፣ ሰልፈር፣ ጨው እና የሃይድሮተርማል ምንጮች መስተጋብር ፈጥረው በሰማያዊ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ እና ብርቱካናማ ቀለማት አካባቢውን አድመቀው ልዩ ውበት ይሰጡታል።
በተቃራኒው ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ የመጨረሻው ከፍታ የሚገኝበት ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ዝቅተኛው ዳሉል እና ከፍተኛው ራስ ዳሽን የሚገኙባት ተፈጥሮ አመዛዝኖ ሁሉንም ስፍራዎች የቸራት ሀገር ነች ማለት ይቻላል።
በመሆኑም በአፋር ክልል የሚገኘውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በምቾት ቱሪስቶች እንዲጎበኙት በማድረግ ሂደት እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል ሆኖ ተገንብቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገግሎት የበቃው ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ሁነኛ የቱሪስቶች የማረፊያና የመዝናኛ ስፍራ መሆን ችሏል።
በ78 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የተገነባው ዘመናዊ ሎጅ ፍልውሃ መዋኛ፣ ሁለት ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ የግል መዋኛ ገንዳ ያላቸው ሁለት ፕሬዚዳንታዊ ቪላዎች፣ 12 እርስ በእርስ የተያያዙ የመኝታ ክፍሎች እና 16 ባለአንድ መኝታ ቤቶችን ያካተተ ነው። በመሆኑም የዚህ ሎጅ መገንባት ለውጭም ይሁን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ምቹና ተመራጭ ማረፊያና የመዝናኛ ስፍራ መሆን እየቻለ ነው።
ኢትዮጵያ የ13 ወራት ፀጋና የብርሃን ጮራ ፈንጥቆ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅባት፤ ለአካባቢ ጥበቃ ምቹ የሆነ ለምለም መሬት ያላት አስደናቂ ሀገር መሆኗ ይታወቃል። የአለማችን ረጅሙ ወንዝ አባይ የሚፈልቅባት፣ ሁሉን አብቃይና የሁሉ መገኛ ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት፣ በታሪክና በባህል የታደለች ሀገር በመሆኗ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን የሃብት ምንጭ በማድረግ ዘርፉ የሀገሪቱን ዕድገት እንዲደግፍ በማድረግ የላቀ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል።