ቀጥታ፡

ስንዴ ከመሸመት ወደ ላኪነት - የኢትዮጵያ የአምራችነት ማሳያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ እመርታ ካስመዘገቡ የግብርና ዘርፎች አንዱ የስንዴ ምርት ነው ። የራሷን ፍጆታ በስንዴ ምርት ማሳካት ባለመቻሏ ለረጅም ጊዜ ከውጭ ታስገባ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ይሄንን ጉዳይ ወደ ታሪክነት ቀይራዋለች።

በየዓመቱ እስከ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ በማድረግ የስንዴ ምርትን ወደ ሀገር ውስጥ ስታስገባ የነበረው ታሪክም እንዲሁ ተለውጧል።

የተለመደውን አካሄድ የቀለበሰና የስንዴ ልማቱን በውጤት ያጀበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ ስንዴን በበጋና በክረምት በስፋት በማልማት የሃገር ውስጥ ፍጆታ በማሟላት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲሁም ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪን በማዳን በስንዴ ልማት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

ቀደም ሲል በአነስተኛ ማሳና በተበጣጠሰ መልኩ ይከናወን የነበረውና የክረምት ዝናብ ጥገኛ የነበረው የምርት ሒደት አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ተቀይሮ የመስኖ ስንዴ በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚከናወን መደበኛ ስራ ሆኗል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ማሳዎች ከተለመደው ኋላ ቀር የግብርና ዘዴዎች በመላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችም እየተተገበሩባቸው ነው። የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከመጠቀም ባለፈ የግብርና ሜካናይዜሽን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለመሸፈን የሚያስችል አቅም እንዲፈጠር አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የስንዴ ፕሮግራም ምርታማነትን በመጨመር፣ የመስኖ ሥርዓትን በማስፋት፣ የዘር አቅርቦት ሥርዓትን በማጠናከር ብሎም በዋና ዋና አካባቢዎች አነስተኛ አርሶ አደሮችን በመደገፍ የሀገራችንን ራስን የመቻል ጉዞ ግብ ላይ የተመሠረተ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በምስራቅ ሐረርጌ ቆላማ አካባቢዎች እየለማ የሚገኝ የበጋ ስንዴ ልማትን በጎበኙበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት መሬት ጦም ማደር የለበትም ብለን አስበን የጀመርነው ስራ እያስገኘ ያለው ፍሬ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው ማለታቸው አይዘነጋም።  

በስንዴ ልማት የተገኘው እመርታ ፈጣን እና አስደማሚም ነው። በጣም ዝቅተኛ የነበረው የስንዴ ማሳ የመስኖ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈጣን እድገት እያሳየ ነው ። ለምሳሌ በ2012 ዓ.ም 20 ሺህ ሄክታር ብቻ በነበረው የመስኖ ስንዴ ልማት 600 ሺህ ኩንታል ምርት ተሰብስቦ ነበር። ይሄ ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ከማስመዝገቡም በላይ ምርታማነትን በተጨባጭ ለውጦታል ።

የመስኖ ስንዴ ልማት በ 2017 ዓ.ም. ምርት ዘመን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሔክታር ያደገ ሲሆን ከ 128 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ይሄ እንግዲህ የስንዴ የመስኖ ልማቱ ማሳያ ነው የመኸር ምርቱንም ስንመለከት በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በ2017 ምርት ዘመን ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን ያሳያል።

በምርት ረገድም ከ53 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማድረግ ተችሏል። በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት በስንዴ የለማ መሬት 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በመሸፈን 280 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል፡፡

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከውጭ ለምታስገባው ስንዴ ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬም ሙሉ በሙሉ ማዳን ተችሏል።

በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ስኬታማ ኢኒሼቲቭ ላደረጉት መሪነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን ሮም የተከበረውን የአለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት አግሪኮላ ሜዳሊያ ሽልማት ጥር 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ማግኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም