ኢትዮጵያ- በተመድ የአፍሪካውያን የፅናት ድምፅ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ- በተመድ የአፍሪካውያን የፅናት ድምፅ
81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች፣ የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች እና የምጣኔ ሀብት ተፅዕኖዎች በበረቱበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በኒውዮርክ በመካሄድ ላይ ነው።
ኢትዮጵያም በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተመራ ልዑክ በጉባኤው በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች።
ጉባኤው በዋናነት ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማፋጠን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መታገል፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማትን አወቃቀር ማሻሻል ላይ አተኩሮ እየመከረ ይገኛል።
በዚህ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ሚና የገዘፈ ነው። ተመድ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁኑ የሪፎርም አጀንዳ ድረስ ሁነኛ የአፍሪካ ድምፅ ሆኖ የመቀጠል የታሪክ አደራን የመወጣት የፀና ጉዞ ነው።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት ብቸኛዋ ነፃ የአፍሪካ ሀገር በመሆን የሳን ፍራንሲስኮውን ቻርተር ከፈረሙ 51 ሀገራት አንዷ ነበረች። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በነበሩበት በዚያ ጨለማ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በተመድ መድረክ ከራሷ ባለፈ የሙሉ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ነፃነትና እኩልነት ስትጠይቅና ስትሞግት ቆይታለች።
ለዓለም ፍትሐዊ መርህ የታገለችው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሠረት አሰባሳቢ ኃይል በመሆን የተመድ መርሆዎች በአፍሪካ ምድር እንዲሰርፁ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለች።
ኢትዮጵያ የተመድ የጋራ ደህንነት መርህን በተግባር በማዋል ረገድ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነች። በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን የተሰማሩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ባሳዩት ፅናት፣ ሙያዊ ብቃት፣ ጀግንነትና ዲሲፕሊን የሀገሪቱን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ በወርቅ ቀለም አጽፈዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላም አስከባሪ ኃይል ለዓለም አቀፍ ሰላም በማዋጣት ከአፍሪካና ከዓለም በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ነች።
በአሁኑ ወቅት በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በጎላ ሁኔታ እየተንጸባረቀ ያለው ዋና አጀንዳ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም ነው። ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያላት አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እና ድምፅን በድምፅ የመሻር የቬቶ ፓወር መብት የላትም።
ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ በደል ለማረም በመሪዋ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ተገቢ ውክልና እና ቬቶ ፓወር እንዲኖራት የአፍሪካን ድምፅ በተደጋጋሚ አሰምታለች። በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችም እየሞገተች ትገኛለች። አሁን ላይ የአፍሪካን አጀንዳ ተመድን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት አጀንዳውን ተቀብለውታል።
በሌላ በኩል፣ አፍሪካ ለዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመርና ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ የጉዳቱ ዋነኛ ሰለባ ነች።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሯ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሥርዓት የመገንባት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አርዓያነቷን በተጨባጭ እያሳየች ትገኛለች። እንዲሁም በተመድ መድረክ አፍሪካ የሚገባትን የአየር ንብረት ፋይናንስና ድጋፍ በፅናት በመጠየቅ ላይ ትገኛለች።
በተጨማሪም የበለፀጉ ሀገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የታዳጊ ሀገራትን የብድር ጫና እና የልማት ፍላጎት ግምት ውስጥ ያጣጣመ አሰራር እንዲከተሉ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የጋራ አጀንዳ በግንባር ቀደምትነት እያንጸባረቀች ነው።
ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ያስመዘገበቻቸውን ድሎችና ተሞክሮዎች፣ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ያሏትን የብሔራዊ ጥቅምና መሻት አጀንዳዎች ለጉባኤው ታጋራለች ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከተመድ ምስረታ ጀምሮ የነበራት ታሪካዊ መብትና ኃላፊነት፣ ዛሬም ቢሆን በዓለም አቀፍ መድረኮች ለአፍሪካ አህጉር እኩልነት፣ ፍትህና ልማት በሚደረጉ የሪፎርም ትግሎች ውስጥ ፊት አውራሪነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል አድርጓታል።
የዘንድሮው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤም ይህንኑ የኢትዮጵያን የፀና የአፍሪካ ድምፅነት አጉልቶ ያሳያል።