ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን ለዓመታት ስታካሂድ የቆየችው ድርድር ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተቃርቧል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን ለዓመታት ስታካሂድ የቆየችው ድርድር ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተቃርቧል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን ለዓመታት ስታካሂድ የቆየችው ድርድር ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መቃረቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የድርድር ሂደት አጠናቃ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆኗ በአሁኑ ወቅት እያከናወነች ያለችውን ሰፊ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማገዝ የዘላቂ ዕድገቷን ፍጥነት እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።
የአባልነት ሂደቱ በሁለት ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፍሎ በከፍተኛ ትኩረት እየተካሄደ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በባለብዙ ወገን ድርድር ማዕቀፍ፣ ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራት ለቀረቡላት ማክሮ ኢኮኖሚና ከንግድ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በርካታ የድርድር ምዕራፎችን አልፋለች።
በዚህም ሂደቱን ወደ መጨረሻው ረቂቅ የሥራ ቡድን ሪፖርት ደረጃ ማድረስ ችላለች።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ከ17 ሀገራት ጋር የጀመረችውን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር በተመለከተ፣ እስካሁን ከ11 ሀገራት ጋር የተቋጨ ሲሆን ከቀሩት ስድስት ሀገራት ጋር የሚደረገው ድርድርም ውጤታማ በሆነ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ የዚህ ዓለም አቀፍ ተቋም አባል መሆኗ ዘመናዊና የተሻሻለ የንግድ ሥርዓት ለመገንባት በርካታ ዕድሎችን ይዞ ይመጣል።
ሀገሪቱ የዓለምን የንግድ ሥርዓት በሚወስኑ የሕግ ማዕቀፎችና የሕግ አወጣጥ ሂደቶች ውስጥ የራሷን ጥቅም የማስከበር ወሳኝ ሚና የመጫወት ዕድል ታገኛለች።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች የሚተገበሩ አሠራሮች አድልኦ አልባና ተገማች እንዲሆኑ በማድረግ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
የገበያ መዳረሻዎችን ከማስፋፋቱም ባሻገር፣ ሀገሪቱ ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወጥታ በዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ በጥልቀት እንድትሳተፍ ያግዛል።
እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሕጎችና አሠራሮች ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ያጎለብታል።
ከአባልነቱ የሚገኙ ጥቅሞችን በሙሉ ለመጠቀም እንዲቻል፣ ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ሚኒስቴሩ በመረጃው ጠቁሟል።
የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችና የግብርና ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ አስፈላጊ የሕግ ማሻሻያዎችን ማከናወንና ለንግዱ ማኅበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር በስፋት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ይገኙበታል።
በቀጣይም ሂደቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ፣ ለስምንተኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ዝግጁ ከመሆን ባሻገር፣ ከቀሩት ስድስት ሀገራት ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽ ድርድሮችን ማጠናቀቅና የመንግሥት ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች እልባት መስጠት ዋና ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።