የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ትግበራ የዜጎችን የስራ ባህልና የኑሮ ሁኔታ እያሻሻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ትግበራ የዜጎችን የስራ ባህልና የኑሮ ሁኔታ እያሻሻለ ነው
ሀዋሳ፣ መስከረም 13/2019(ኢዜአ)፡- የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ትግበራ የዜጎችን የስራ ባህልና የኑሮ ሁኔታ እያሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ፡፡
የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት በከተሞች ድህነትን ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እያገዘ ይገኛል።
ለተግባራዊነቱም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በከተማ ማፅዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ ልማት እና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ተጠቃሚዎችም የፋይናንስ እውቀት፣ የክህሎት ሥልጠና እና የንግድ መጀመሪያ ድጋፍ አግኝተው የራሳቸውን ቋሚ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያና፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘርፉ አመራሮች እንዳሉት፣ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ትግበራ የዜጎችን የስራ ባህልና የኑሮ ሁኔታ እያሻሻለ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ፣ ፕሮግራሙን በክልሉ በሚገኙ 6 ከተሞች ተግባራዊ በማድረግና የክህሎት ሥልጠና እንዲሁም የመሥሪያ ቦታ በመስጠት በርካታ ዜጎች ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ተጠቃሚዎች በከተሞች ጽዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ አሻራ ልማትና በሌሎች የአካባቢ ልማት ሥራዎች በመሳተፍ ሀብት አፍርተው መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ ተገኝ በበኩላቸው፣ በክልሉ በሁለት ከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ18 ሺሕ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ የዜጎችን የቁጠባና የሥራ ባህል በመቀየር ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ማድረጉንና ጽዱ ከተሞችን ለመፍጠር የሚያግዙ የአካባቢ ልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሞላ ናቸው።
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ተጠቃሚዎቹ ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ የመሥሪያና የመሸጫ ሼዶችን በመገንባት 292 ኢንተርፕራይዞችን ማደራጀት ተችሏል ብለዋል።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ በ88 ከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ያሸጋገረ ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙን ከአረንጓዴ አሻራ፣ ጽዱ ኢትዮጵያ፣ ተፋሰስና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጨምሮ ከሌሎች ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ጋር አሰናስሎ በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም አስረድተዋል።
ለሦስተኛው ምዕራፍ የፕሮግራም ትግበራ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ መመደቡን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ከ318 ሺሕ በላይ ዜጎችን ለማሳተፍ እንደታቀደም ጠቁመዋል።
ተጠቃሚዎችን በአካባቢ ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ጎዳና ላይ የወጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቤተሰብ በመቀላቀል ሥራ ላይ ለማሳተፍ ትኩረት መደረጉንም አብራርተዋል።