በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የስነልቦና ዝግጅት አድርገናል-ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የስነልቦና ዝግጅት አድርገናል-ተማሪዎች
ሮቤ፤መስከረም 13/2019(ኢዜአ)፦ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ የትምህርት ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን የስነ-ልቦና ዝግጅት በማድረግ ወደ መደበኛ የትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ፤ በክረምቱ ወራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን ለመፍጠር በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ነባር ተማሪዎችን መቀበሉን አስታውቋል።
ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሀሰን ሙክታር በሰጠው አስተያየት፤ በክረምቱ ወራት በአካባቢው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን አስታውሷል።
በዩኒቨርሲቲው የተከናወኑት የገጽታ ግንባታና ለትምህርት አጋዥ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ለትምህርታቸው አዲስ መነሳሳትን እንደፈጠሩላቸውም አመልክቷል።
በክረምቱ ወራት የግቢው ውበትና የመኝታ ክፍሎች ሁኔታ እንዲሻሻል መደረጉ ምቹ የመማር-ማስተማር አካባቢን እንደሚፈጥር የተናገረው ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ መሐመድ አሊ ነው።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለትምህርታቸው ቅድሚያ በመስጠትና በትጋት በመማር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩም ተናግሯል።
ተማሪ ሀቢባ አህመድ በበኩሏ፤ በክረምቱ እረፍት ወቅት በአካባቢዋ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ጊዜዋን በአግባቡ ማሳለፏን ተናግራለች።
በአካባቢያቸው ለተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አስተዋጽኦ ማበርከታቸው መልካም ተሞክሮ እንደፈጠረላቸውም ተማሪ ሀቢባ አክላ ገልጻለች።
ተማሪዎቹ እንደገለጹት በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ የትምህርት ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን የስነ-ልቦና ዝግጅት በማድረግ ወደ መደበኛ የትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል።
ለተማሪዎቹ አቀባበል ያደረጉት የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ ተቋሙ በክረምቱ ወራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ምቹ የመማር-ማስተማር ሁኔታን ለመፍጠር በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ነባር ተማሪዎቹን መቀበሉን ገልጸዋል።
በተለይም የግቢ ውበትን የመጠበቅ፣ የመኝታ ክፍሎችን የማሰናዳት እንዲሁም የቤተ-መጻሕፍትና ሌሎች አጋዥ አገልግሎቶችን የማሻሻል ተግባራት መጠናቀቃቸውን በማመልከት፣ ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስገንዝበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ-ግብር ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ ያሉ 3 ሺህ 700 የሚሆኑ ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር-ማስተማር ሥራውን መጀመሩም ተመልክቷል።