"አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመጨረሻ ፈጠራ ወይስ የፈጠራ መጨረሻ?" በሚል ርዕስ በሰለሞን ሙሉጌታ የተጻፈ መጽሐፍ ዛሬ ለንባብ በቃ - ኢዜአ አማርኛ
"አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመጨረሻ ፈጠራ ወይስ የፈጠራ መጨረሻ?" በሚል ርዕስ በሰለሞን ሙሉጌታ የተጻፈ መጽሐፍ ዛሬ ለንባብ በቃ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- "አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመጨረሻ ፈጠራ ወይስ የፈጠራ መጨረሻ?" በሚል ርዕስ በሰለሞን ሙሉጌታ የተጻፈ መጽሐፍ ለንባብ በቃ።
"አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመጨረሻ ፈጠራ ወይስ የፈጠራ መጨረሻ?" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መፅሀፍ ሲሆን፤ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ የጸሀፊው ቤተሰቦችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ተመርቋል።
የመጽሐፉ ጸሀፊ ሰለሞን "ቴክ ቶክ ዊዝ ሰለሞን" በሚል ርዕስ በሚያዘጋጀው ፕሮግራም የቴክኖሎጂ ዜናዎችን፣ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችና ሳይንቲስቶች በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በአዲስ አበባ ባቋቋመው የቴክኖሎጂ የፈጠራ ማዕከልም ወጣት የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ስታርታፖችን በመደገፍ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ዲጂታል ሽግግርን ማፋጠን እንዲሁም ለቴክኖሎጂው ዕድገት የበኩሉን ሚና እየተወጣም ይገኛል።
ሰለሞን ሙሉጌታ ያስመረቀው መጽሐፍ በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ሽግግር ውስጥ ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ መሆኑ ተጠቁማል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መጽሐፉ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በቀላል ቋንቋ የሚያስረዳ በመሆኑ ግንዛቤን ለማስፋት መሰረት ይጥላል ብለዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጥቅምና ስጋቶች በአግባቡ እንደሚተነትን ጠቁመው፤ በዘርፉ ውጤታማ ሆኖ ለመዝለቅ አመላካች ሃሳቦች የተካተቱበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጂኦ ፖለቲካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ያለውንም ቦታ በተመለከተ ጥልቅ ጽንሰ ሃሳብ የያዘ በመሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የስነ አዕምሮ ሀኪሙ ዶክተር ምህረት ደበበ በበኩላቸው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ትምህርት፣ ጤና፣ ፖለቲካ፣ ወታደራዊ መስኮችን ጨምሮ በሁሉም የህይወት መስኮች በሚባል ደረጃ ሚና መጫወት መጀመሩን አንስተዋል።
ስለሆነም ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መራቅ እንደማይቻል አንስተው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንዴት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ልንጠቀም ይገባል የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
መጽሐፉ ለእነዚህ ጉዳዮች በቂ ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ከሞራል ጋር ባስተሳሰረ መልኩ የመጠቀምን አስፈላጊነትንም መጽሐፉ እንደሚዳስስ ጨምረው አብራርተዋል።
የመጽሐፉ ጸሀፊ ሰለሞን በበኩሉ፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ የህክምና፣ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የህልውና ጥያቄ መፍቻ ቁልፍ እንደሚሆን አብራርቷል።
የስራ ዕድል ፈጠራ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን በምን መልኩ ሊቃኝ ይገባል? የአፍሪካ ሀገራትም በምን መልኩ ሊያዩት ይገባል? የሚለውንም ጥያቄ በማንሳት መጽሐፉ እንደሚያብራራ ገልጸዋል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ውስጥ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ እንዴት ይሆናል? የሚለው ጉዳይ በመጽሐፉ ውስጥ መካተቱን ጠቁሞ፤ ከዘርፉ የአፍሪካን የተጠቃሚነት ድርሻ ለማሳደግ በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል ነው ያለው።
ጸሀፊው ሰለሞን ሙሉጌታ ከዚህ ቀደም "ግርመተ ሳይቴክ" የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።