ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማቱ የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር ምቹ ሁኔታ እና ድምቀትን የሚጨምር ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 13 /2019(ኢዜአ)፡- በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ የመዝናኛ ስፍራዎች የመስቀል ደመራ  በዓልን በልዩ ሁኔታ ለማክበር ምቹ ሁኔታና ድምቀትን የሚያላብስ መሆኑን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ለኢዜአ እንደገለጹት፤በከተማዋ የመስቀል ደመራን በዓል በድምቀት ለማክበር  አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል።


 

በከተማዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡት የመዝናኛ ስፍራዎች  ለጎብኚዎች ምቾትን  ከመስጠት በተጨማሪ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበርና ውበትን ለማላበስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የገለጹት።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የመስቀል በዓል ከአለም የቱሪዝም ቀን ጋር አስተሳስሮ በማክበር የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በበዓሉ ለመታደም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እየገቡ በመሆናቸው ጎብኝዎችን በተሻለ መንገድ ለማስተናገድ ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን ነው የገለጹት። 


 

ህብረተሰቡ ወደ ከተማዋ የሚመጡ  እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት በማስተናገድ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያና ሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች የሚያካሂዱትን የእግር ኳስ ጨዋታና የጣና ፎረም ስብሰባን በማስተናገድ ከተማዋ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነቷን ለማሳደግ  እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የዓባይ፣ ጣናና የባህር ዳር አካባቢ አስጎብኚዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ማስተዋል ዘለቀ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለመጎብኝትና በዓሉን ለማክበር  የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከበዓሉ አከባበር በተጨማሪ እንግዶቹን በጣና ውስጥ የሚገኙ ደሴቶችን፣ ገዳማትን፣ የጢስ አባይ ፏፏቴንና ሌሎች የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን በማስጎብኘት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የማህበሩ አባላት በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት እሴትን መሰረት በማድረግ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በአስጎብኝነት ስራ የተሰማሩት አቶ አበበ ያረጋል በበኩላቸው፤ ቱሪስቶችን በመልካም መስተንግዶ በማስጎብኘት የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንዲችሉ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት የመዝናኛ ሰፍራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም