በጉራጌ ዞን የበዓል ገበያ የእርድ እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ ምርቶች በበቂ መጠን ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን የበዓል ገበያ የእርድ እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ ምርቶች በበቂ መጠን ቀርበዋል
ወልቂጤ ፤ መስከረም 13/2019(ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል ገበያ የእርድ እንሰሳት እና አስፈላጊ ምርቶች በበቂ መጠን መቅረባቸውን ሸማቾች እና ነጋዴዎች ገለፁ።
በጉራጌ ዞን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል መስቀል ተጠቃሽ ነው።
መስቀል በጉራጌ ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የተቀያየመ የሚታረቅበት፣ የተራራቀና ወዳጅ ዘመድ የሚገናኝበት፣ ጋብቻ የሚፈፀምበት የፍቅርና የአንድነት ታላቅ በዓል ነው።
ለዚህ ወቅት የሚሆኑ ቤት ውስጥ ከሚዘጋጁት በተጨማሪ ገበያ ላይ የሚሸመቱት በርካታ ምርቶች ናቸው።
ኢዜአ በተለያዩ በጉራጌ ዞን በሚገኙ የእርድ እንስሳት ፣ የቤት መገልገያ እና ባህላዊ እቃዎች በስፋት ግብይት በሚከናወንባቸው ገበያዎች ቅኝት አድርጓል ።
ከእነዚህም መካከል በወልቂጤ ከተማ ጉብሬ ገበያ የእርድ ሰንጋ ሲገዙ ያነጋገርናቸው አቶ ተክሉ ብዛኒ እንዳሉት፤ ለበዓሉ ሁሉም እንደየ አቅሙ መግዛት የሚያስችለው የእርድ እንስሳት ቀርበዋል ።
ከወትሮው የዋጋ ጭማሪ ቢኖረውም እሳቸውም በአቅማቸው ልክ የሚፈልጉትን ሰንጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በእዣ ወረዳ አገና ገበያ የእርድ ከብት ሲሸጡ ያገኘናቸው ጀማል ፈረጃ እና ተረጋ በረከት በበኩላቸው፤ በቂ የእርድ እንስሳት አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በህብረተሰቡ ተፈላጊ የሆኑ የእርድ እንስሳት ካለፈው ዓመት በተሻለ ለገበያ መቅረባቸውን ተናግረው፤ የዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም ሁሉም በአቅሙ ልክ ግብይት መፈፀም የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
በአገና ገበያ የእደ ጥበብ ውጤቶች ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ባድወርቅ ገብሬ ለመስቀል ወቅት ተፈላጊ ምርቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል።
እሳቸውንም ሆነ የህብረተሰቡን አቅም ባማከለ መልኩ ምርቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን በበኩላቸው የግብርና፣ የኢንደስትሪ ምርቶች እና የእርድ እንስሳት ከአቅራቢ ወደ ሸማቾች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ወደ ገበያ እንዲወጣ መደረጉን ገልፀዋል።
በበዓል ገበያው የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በዚህም ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል።
የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚደረግ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል በተቋቋመው የቁጥጥርና የክትትል ግብረ ኃይል አማካኝነት ህገወጥነትን የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።