ቀጥታ፡

ከበጎ ተግባር እስከ ዘላቂ የልማት ባህል - የክረምት በጎ ፈቃድ ሀገራዊ ዐሻራዎች

የክረምት ወራት በኢትዮጵያ ዝናብና ቅዝቃዜ የሚበዛበት ወቅት ብቻ መሆኑ ቀርቶ፣ የወጣቶች ጉልበት፣ ዕውቀትና አብሮነት የሚፈነጥቅበት የሀገር ትንሣኤ ምዕራፍ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ቀደም ሲል በግለሰቦች በጎ አድራጎትና በትንንሽ ስራዎች ተወስኖ የነበረው እንቅስቃሴ፣ ዛሬ ላይ መዋቅራዊ ቅርፅ ይዞ የሀገሪቱን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥን ዘላቂ የልማት ባህል ለመሆን በቅቷል።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ በማስተባበር «ለኢትዮጵያ ከፍታ» የተነደፈውን ብሔራዊ ራዕይ በመሬት ላይ በተግባር የሚያስመሰክር ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ሆኗል።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የሀገሪቱን የማንሰራራት ዘመን በግልጽ ከሚያሳዩ ብሔራዊ ንቅናቄዎች አንዱ ሆኗል።

የዚህ ብሔራዊ ንቅናቄ ዋና ሞተሮች የሆኑት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው።

ወጣቶቹ ከክልል ክልል በመዘዋወር የሚያከናውኑት ወሰን ተሻጋሪ አገልግሎት ከልማቱ ባሻገር፣ በህዝቦች መካከል የማይበገር ወንድማማችነትን፣ ትስስርንና አብሮነትን እያጠናከረ ይገኛል።

ይህም በጎ ፈቃደኝነት የጂኦግራፊያዊና የማህበራዊ ወሰኖችን በመሻገር የአንድነትና የአብሮነት ገመድ መሆኑን አሳይቷል።

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተለመደው የአቅመ-ደካሞች ቤት እድሳት ተሻግሮ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶችን በስፋት አቅፏል።

ለአብነትም በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተካሄደው ንቅናቄ ብቻ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ነፃ የሕክምና፣ የምክርና የወባ መከላከል አገልግሎት ማግኘት ችለዋል።

በወጣቶች ጉልበት፣ ዕውቀትና የሙያ ድጋፍ የተከናወኑት እነዚህ ሥራዎች ለመንግሥትና ለማህበረሰቡ በቢሊዮን የሚቆጠር አገራዊ ሀብት ማዳን ችለዋል።

ይህ ንቅናቄ ዜጎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ለአቅመ-ደካሞች መጠለያ እንዲገነቡ፣ ማዕድ እንዲያጋሩ እና ደግነትን የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዲያደርጉ ትልቅ መሰረት ጥሏል።

በተለይም ከመንግሥት የገጠር ኮሪደር ልማት ጋር ተቀናጅቶ የተካሄደው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለተጋለጡ ወገኖች ዘላቂ እፎይታን ሰጥቷል።

በተጨማሪም በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ በእርሻ ደጋፊነት እና በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፎች የነበረው ተሳትፎ የንቅናቄውን ሁለንተናዊነት አጎልቶታል።

ይህ አገራዊ እንቅስቃሴ አገራዊ ልማት በበጀት እጥረት ምክንያት ሊገታ እንደማይችልና በህዝብ ሀብት፣ ጉልበትና ዕውቀት ሊረጋገጥ እንደሚችል በተግባር ያሳየ ነው።

ለቀጣይ ምዕራፍ አገልግሎቱን የበለጠ ተቋማዊ በማድረግ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ እና የተሳትፎ አድማሱን ከፍ በማድረግ የትውልድ ግንባታ አካል ማድረግ ቁልፍ አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በወጣቶቿ ክንድና በሕዝቧ አብሮነት አልፋ ከፍታዋን ማረጋገጥ እንደምትችል ያሳየችበት የድል፣ የትውልድ ግንባታ እና የማንሰራራት ምዕራፍ ማሳያ ሆኖ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም