ቀጥታ፡

ሀገር ያጸና ጀግና የመከላከያ ሠራዊት!

ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያዩበት መነጽር እጅግ ልዩ ነው። የገዘፈ ምስል በታላቅ ግርማ ሞገስ የሚመለከቷትን አገራቸውን በታላቅ የሀሳብ ልዕልና አክብረው፣ አስከብረውና እያከበሩት የሚኖሩት ምሰጢሩ የሚመነጨው በአእምሯቸው ካለው ሀገራዊ ምስል ነው። 

በታላቅ የሀሳብ ልዕልና የተገነባ የአገር ፍቅር ከጥንት ጀምሮ ያለ፣ የሚኖርና ለዘመናት የሚዘልቅ ነው። ይህ የኢትዮጵያዊነት መሰረት ነው እንግዲህ አገራቸውን በሉዓላዊነት ጠብቀው እንዲኖሩ ያደረገው። የጀግንነት ምስጢራቸው እና የነጻነት ልዕልናቸው ከዚህ በቀላሉ ከማይነካ ትስስራቸው የሚመነጭ ነው።

የውጭ ጠላቶቻቸው ጦር ሰብቀው፣ ገስግሰውና “ድል የእኛ ነው” ብለው ሲመጡም አፍረውና ተዋርደው እንዲመለሱ የሚያደርጋቸው በጠንካራ መሰረት ላይ በተገነባው የሀገር ፍቅር ስሜታቸው፣ በደምና ባጥንታቸው መከታ ነው። ደርቡሽ ቢመጣ አፍሮ የተመለሰው፣ ግብጽ ጦሯን አሰልፋ አገር ለመውረር ደጋግማ ብትመጣ አፍራና ተሸማቃ የሄደችው በኢትዮጵያዊያን ጠንካራ ክንድ ነው። 

ጣሊያን የቀኝ ገዥነት ህልሙን እውን ሊያደርግ በወቅቱ በያዛቸው ድንቅ መሳሪያዎች ተማምኖ ባሕር አቋርጦ ገስግሶ ቢመጣም፣ በአራት ሰዓታት ውጊያ ዓለምን ባስደመመ ቅጽበት ድል ተነስቶ፣ ወታደሮቹ ሞተው፣ ከፊሎቹ ተማርከው የተመለሱት በጀግንነት በተዋጓቸው ኢትዮጵያዊያን ነው።

ይህ የታሪክ ልዕቀት የተመዘገበው ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነው አይደለም። ለአብነት ያህል፣ አስደናቂው የዓድዋ ድል ሲመዘገብ ኢትዮጵያውያን በውስጥ የራሳቸው ችግር ነበረባቸው፤ ረሃብ ያስከተለው ድርቅ ሀገራዊ ችግሩን አግዝፎት ነበር። ይህ እውነታ ግን ለኢትዮጵያውያን አንድነትና ጠላትን ድል ለመንሳት አላገዳቸውም፤ ነጻነታቸውን አስቀጥሎ ለማስኬድም ተግዳሮት አልሆነም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት “ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከነፃነት፣ ከክብር፣ ልቆ ከመታየት፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ህዝብ ራስን ከመሰዋት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው” በማለት የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና ለሀገራቸው መስዋዕት ስለመሆን ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያውያን ጀግንነት መገለጫው በውስጣቸው እርስ በርስ በሃሳብ ሊለያዩ፣ ሊጋጩና አንዱ ሌላውን ሊቆጣ ይችላል፤ ይህ ተፈጥሯዊ ነው። ሆኖም ጠላት ሲመጣ የራሳቸውን የውስጥ ችግር ወደ ጎን በመተው ለአንድ ዓላማና ግብ ወደ ፊት ይገሰግሳሉ።

ሌላውን የማሸናፍ ምስጢራቸው የሚፈለቀቀው ከዚህ እውነት ነው። የቅርቡን የሱማሊያ ወረራ መነሻ እንኳን ብንወስድ፣ “ኢትዮጵያውያን በለውጥ ማዕበል እየተመቱ ነው፣ በሰሜን ችግር አለባቸው፤ ስለዚህ ወረራ በመፈጸም እናጥቃ፣ አዋሽን እንሻገር” በሚል የተሳሳተ ስሌት የተጀመረውን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ከአርሶ አደር እስከ ተማሪ በአንድነት በመዝመት ድል ነስተው አስወጥተውታል። ይህ ሲባል ግን ባንዳ አልተፈጠረም፣ የሀገሩን ጥቅም ለግልም ሆነ ለቡድን ፍላጎት አሳልፎ የሚሰጥ የለም ማለት አይደለም።

“በታሪካችን በሙሉ ግን ሊነኩን የመጡትን ከቅርብም ከሩቅም አሳፍረን መመለስ ደግሞ ተግባራችን፣ መገለጫችንና ማንነታችን ነው። አንነካም፤ ከመጡብን ግን ማንንም፣ ማንንም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር አንደራደርም። ማንም ኢትዮጵያን መድፈር ቢፈልግ አንዴ ሳይሆን አስር ጊዜ ማሰብ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን የምንችለው አንዱና ትልቁ ነገር ራሳችንን መከላከል ነው” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያስቀመጡትን ሀሳብ እዚህ ላይ ማንሳት ይቻላል።

የኢትዮጵያውያን የጦር ውሎ ጀግንነት ለሀገራቸው ካላቸው ቀናኢ የሀሳብ ልዕልና የሚመነጭ ነው። ለእነርሱ ሀገር ማለት ልዩ ትርጉም አለው። ከሁሉም ነገር በላይ የገዘፈና ጠንካራ መገለጫ ያለው፣ ጠላቶች መጥተው ሲጋጩት ተሰባብረው የሚበታተኑበት ልዩ ምስጢር ያለው ነው። 

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር፣ እንድትበታተን በመስራት ታሪክ ሊያደርጓት ብዙዎች ጥረዋል። ነገርግን ጠላቶቿ የተላተሟት የገዘፈ ልዕለ ሀሳብ ከሚመራው ኢትዮጵያዊ ጋር ነው። ድል ነስቷቸው የሚመለሱትም ይህንን ግዝፈት ቀለል አድርገው በማየታቸው ነው።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአንድ ወቅት እንደገለጹት፤ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶቻችን ሀገራችንን ከምስራቅ አፍሪካ ካርታ ለማጥፋት ለዘመናት ቢሞክሩም አልቻሉም።

ይህ የታሪክ ድርሳናት የሰነዱት ጠንካራ የሉዓላዊነት ልዕለ ሀሳብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚገዛለት መሆኑን የተረዱት ጠላቶች፣ ለራሳቸው ጥቅምና ለቡድን ፍላጎት የተንበረከኩ፣ ራሳቸውን ለጥቅም አሳልፈው በሰጡ ባንዳዎች በኩል እጃቸውን አስረዝመው መምጣታቸው አልቀረም። 


 

21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም እጅግ በተሳሰረችበትና ጥብቅ ግንኙነት በፈጠረችበት ምህዳር ላይ፣ ጠላቶቻችን አልተኛም ብለው ስምሪት በሰጧቸው ባንዳዎች በኩል እየመጡ ነው።

“ስለዚህ በእጅ አዙር መዋጋትን መርጠው በራሳችን ባንዳ ልጆች እየሞከሩ ነው። ምክንያት እየደረደረ ጫካ የገባው ባንዳ፣ ስደተኛ ባንዳ እና ሰርጎ ገብ ባንዳ የገዛ ሀገሩን አደጋ ላይ ለመጣል የሚወራጨው፣ በታሪክ የለመደውን የውጭ ጠላቶች ጉዳይ ተጭኖ ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ ተግባር መተዳደሪያው ስላደረገው ነው።" በማለት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የገለጹት ሐሳብ የኢትዮጵያ ጠላቶች በቀጥታ ሳይሆን በእጅ አዙር ለመውጋት ተኝተው እንደማያድሩ ማረጋገጫ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሏን በሪፎርም ጠንካራና የማይበገር በማድረግ ለማንኛውም ጉዳይ ዝግጁ አድርጋለች። የመከላከያ ኃይሏን ዘመኑን በሚዋጅ ዘመናዊነት እየገነባች ነው። ሰላሟን ለማረጋገጥና በአስተማማኝ ኃይል ላይ ለመሆን ኢኮኖሚዋን እያሳደገች ነው። ከውጭው ዓለም ጋር ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነትም በከፍታ ላይ ይገኛል።

የመከላከያ ሰራዊት በተግባር የተፈተሸ ኃያልነቱን ያረጋገጠ፣ የማድረግ አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ፣ በጠላት ፊት ጀርባውን መስጠት የሚባል ታሪክን የማያውቀው እና አስደናቂ ታሪክ በደሙ የጻፈና የሚጽፍ የማይበገር ኃይል ያለበት ነው።

መከላከያ ሰራዊት  በየትኛውም ቦታና ጊዜ ከመንግስት፣ ከህዝብና ከተቋሙ የሚሰጡትን ማንኛውንም ግዳጅ ከትናንት በላይ በሆነ በላቀ ደረጃ ለመወጣት በከፍተኛ ዝግጁነት ላይ ይገኛል።

ዛሬ ጠላቶቻችንና እግራቸው ስር ሆነው ለሚላላኩት የምንለው፦ “ኢትዮጵያን ተዋት፤ 21ኛውን ክፍለ ዘመን ለመዋጀት ትስራ፤ በጦርነት ስም አትጎትቱ፤ ማጣፊያው እንዳያጥራችሁ” የሚል ነው።

“ኢትዮጵያን አትንኳት፤ ኢትዮጵያ መልማትና መበልፀግ ተፈልጋለች፤ በግራም በቀኝም ኢትዮጵያን ለማዳከም የምትሰሩ እኛን ከመንካታችሁ በፊት ደጋግማችሁ አስቡበት” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገለጹት ሐሳብ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የጸና አቋም በግልጽ ያሳያል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም