ቀጥታ፡

ከመሸመት ወደ ማምረት- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስኬቶች

የአንድ ሀገር ታላቅነትና የማንሰራራት አቅም የሚለካው በገጠሟት ፈተናዎች ስፋት ሳይሆን፣ እነዚያን ፈተናዎች ወደ ልማትና ዘላቂ ስኬት ለመቀየር በሚወሰዱ ቆራጥ አገራዊ እርምጃዎች ነው በመባል የሚታወቀው እውነት በኢትዮጵያ እውን እየሆነ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ አያሌ መዋቅራዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን አልፋ የተጓዘች ሀገር እንደመሆኗ መጠን፤ በአሁኑ ወቅት የነበሩባትን ማነቆዎች ወደ አዲስ ዕድል በመቀየር ላይ ትገኛለች።


 

ይህ ሂደት በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመሬት ላይ በሚታዩ ዘላቂ ታላላቅ ፕሮጀክቶችና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች እውን እየሆነ ይገኛል።

ይህንን እውነታ በተግባር ከሚያሳዩ ታላላቅ ሀገራዊ መርሐ ግብሮች መካከል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።

ንቅናቄው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለመፍታት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማዘመን ያለመ ነው።


 

መርሐ ግብሩ በአጭር ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ ደህንነት፣ የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥቷል።

ይህ ንቅናቄ በይፋ የተጀመረው በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ሲሆን፤ ዋነኛ ዓላማውም በኢንዱስትሪ ዘርፉ ይስተዋል የነበረውን የቅንጅት ማጣት፣ የፋብሪካዎችን መዘጋት እና እጅግ ዝቅተኛ የነበረውን አማካይ የማምረት አቅም ለማሻሻል እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቀነስ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ነው።

ከዚህ አኳያ ንቅናቄው የታለመለትን ግብ በማሳካት ረገድ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ ነው።


 

በአሁኑ ወቅት ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ተዘግተው የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን፣ ከ14 ሺህ 500 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ከ350 በላይ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተዋል።

ይህም የኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም 67 በመቶ የተሻገረ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች የምርት ድርሻም ከ30 በመቶ ወደ 45 በመቶ አድጓል።

ከፋይናንስና ከምርት ዕድገት ባሻገር፣ ንቅናቄው ለብዙ ቁጥር ላላቸው ዜጎች፣ በተለይም ለወጣቶችና ለሴቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በተጨማሪም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በተደረገ ቅንጅት የኢንዱስትሪዎችን የቴክኖሎጂ ፍላጎት የሚያሟላ የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራ ጎን ለጎን እየተከናወነ ይገኛል።

በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ አልባሳትን እና የግብርና ማቀነባበሪያ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።


 

ከንቅናቄው መጀመር አንስቶ በየዓመቱ በሚዘጋጁት የገበያ ትስስሮችም በአምራቾች እና በገዢዎች መካከል ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውል ተፈጽሟል።

የሀገር ውስጥ ምርቶችን ተወዳዳሪ ለማድረግ በኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩትና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካኝነት ለአምራቾች የቴክኒክና የሎጅስቲክስ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ይህም የሀገር ውስጥ ምርቶች በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያዎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትና እምነት እንዲጨምር አድርጓል።

ወደፊት የመንግስት ትኩረት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችና የረጅም ጊዜ ብድር ማመቻቸት ላይ ያተኩራል። ምርቶችን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ የወደፊቱ ዋና አቅጣጫ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመሸመት ወደ ማምረት እና ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል የተደረገ ትልቅ የኢኮኖሚ አብዮት በመሆኑ፣ ፈተናዎችን ወደ ልማት በመቀየር እያንሰራራች ያለችውን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚዋ የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያደርጋት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም