ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል - አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር)

አዳማ፤ መስከረም 13/2019(ኢዜአ)፡-የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘለቄታዊ የልማት ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ስምንት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ዘመናዊ የአዳማ ከተማ የተቀናጀ የህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የሚገነቡ የከተሞች መሠረተ ልማቶች የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ ጎልቶ የሚታይ ድርሻ አላቸው።

በአዳማ ከተማ የተገነባው ዘመናዊ መናኸሪያ የዚሁ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የማህበራዊ ትስስር ማሳያ እንደሆነም አብዱልአዚዝ  (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የክልሉ ሌሎች ከተሞችም በአዳማ እየተመዘገበ ካለው ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ልምድ በመውሰድ ከተሞቻቸውን መለወጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአመራር ሰጪነት ብቃት የሚለካው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለሕዝብ አገልግሎት በማብቃትና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ጥራትና ፍጥነታቸውን ጠብቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ከማል ማሜ በበኩላቸው፤ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ዘመናዊ የሕዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ ግንባታን አጠናቆ ለአገልግሎት በማብቃቱ የትራንስፖርት ስምሪቱን በማዘመን ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የተገነባው መናኸሪያ የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥና በክልሉ የተጀመረውን የትራንስፖርት ዘርፍ ሪፎርም የሚያቀላጥፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ከማል፤ ኤጀንሲው መናኸሪያዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማደራጀትና አሰራራቸውን የማዘመን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ እንደገለጹት፤ የተገነባው ዘመናዊ መናኸሪያ የከተማዋን የትራንስፖርት ስምሪት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀላጥፍ ነው።

በከተማዋ የተቀናጀና ዘመናዊ የትራንስፖርት ስምሪት ሳይኖር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማፋጠን እንደማይቻል የገለጹት ከንቲባው፤ አስተዳደሩ በስምንት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን የመጀመሪያው ምዕራፍ የመናኸሪያ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል።

ይህ የመናኸሪያ ፕሮጀክት የ«ስማርት አዳማ» ፕሮግራም አካል መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አቶ ሃይሉ፤ ዘመናዊ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ስርዓትን በመተግበር ሀብትን ለሕዝብ ልማት ለማዋል የተሰራው ስራ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል። 

መናኸሪያው በአንድ ጊዜ ከአራት መቶ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታር መሆኑንም ከንቲባው አክለው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም