የ"ዮ-ማስቃላ" በዓል እሴቶች የህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር እንዲጎለብት ጉልህ ፋይዳ አላቸው-የበዓሉ ታዳሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የ"ዮ-ማስቃላ" በዓል እሴቶች የህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር እንዲጎለብት ጉልህ ፋይዳ አላቸው-የበዓሉ ታዳሚዎች
አርባ ምንጭ፤ መስከረም 13/2018 (ኢዜአ)፡- የ"ዮ-ማስቃላ" በዓል እሴቶች የህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር እንዲጎለብት ጉልህ ፋይዳ አላቸው ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ፡፡
በዓሉ የ"ዮ-ማስቃላ እሴቶች ለዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሐሳብ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ተወላጆችና ከሌሎች ክልሎች የመጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተጋብዘው የመጡ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፣ የጋሞ የዘመን መለወጫ "ዮ ማስቃላ" በዓል ባህላዊ እሴቶች የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ለማጎልበት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኦሮሚያ ክልል የመጡት አቶ በላይ ሳማሮ፣ የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ከሆነው የጋሞ ማኅበረሰብ ጋር በአንድነት ሆነን በማክበራችን ልዩ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
በዓሉ የሕዝቡን ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ እንድናውቅ፣ ብሎም እርስ በርስ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት እንድንፈጥር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ሆነን ''ዮ-ማስቃላ''ን ማክበራችን በሕዝቦች ዘንድ የሚኖረውን አብሮነት ያጠናክራል ብለዋል።
በዓሉ ወንድማማችነትን የሚያጎለብት መሆኑን የገለፁት ደግሞ ከሲዳማ ክልል የመጡት አቶ ወልደመስቀል ቃናፋ በዓሉ ለሕዝብ አንድነት፣ ለገጽታ ግንባታ፣ ብሎም ተደጋግፈን የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአለባበስ፣ የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም የዕደ ጥበብ ሀብቶች ጎልተው የሚታዩበትና የፍቅር ስጦታ የሚበረከትበት በመሆኑ፣ አካባቢውን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉም አክለዋል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት አቶ ወንድሙ ወደቦ በበኩላቸው፣ በዓሉ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክር በመሆኑ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማውረስ በበዓሉ የሚንጸባረቁትን የጋራ እሴቶቻችንን መጠበቅ አለብን ብለዋል።
የጋሞ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሰላማዊት ቦዳ፣ "ዮ ማስቃላ" የኢትዮጵያ የጋራ ሀብት የሆኑትን የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የሰላም፣ የመቻቻልና የይቅርታ እሴቶችን ያቀፈ የሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ ነው ብለዋል።
በዓሉ አዲስ ዘመንን ከማብሰር ባለፈ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚገናኙበትና ያዘኑ የሚጽናኑበት ልዩ ሁነት ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።