የአዲሱ መንግሥት ምስረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ይካሄዳል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲሱ መንግሥት ምስረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ይካሄዳል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2019 (ኢዜአ):- የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፁ፡፡
አፈ-ጉባኤው ባስተላለፉት መልእክት፤ የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዚሁ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10,438 እጩዎች እንዲሁም ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መሳተፋቸውንም አውስተዋል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ መሆኑ ተደንግጓል።
በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀመር በተደነገገው መሠረት፣ የመንግሥት ምስረታውና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይከናወናል።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መንበር ያገኘው የፖለቲካ ፓርቲ የፌደራሉን ሕግ አስፈጻሚ አካል የሚያደራጅ ሲሆን፣ በሕዝብ የተመረጠው አዲሱ ሕግ አስፈጻሚ አካል በዕለቱ በይፋ ኃላፊነት እንደሚረከብ ገልጸዋል።
ለሥነ-ሥርዓቱ አስፈላጊው ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው፤ መጪው ዘመን የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።