ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለ2019 የትምህርት ዘመን ከ22 ሺህ በላይ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለ2019 የትምህርት ዘመን ከ22 ሺህ በላይ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቋል
ጅማ ፤መስከረም 13/2019 (ኢዜአ)፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2019 የትምህርት ዘመን ከ22 ሺህ በላይ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን ገለጸ።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ ከሚገኙ ቀዳሚ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን፣ በተለይም በማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት እና በሕክምና ዘርፍ የላቀ ስም ያተረፈ ተቋም ነው።
ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በተለያዩ የመደበኛ፣ የማታ፣ የሳምንት መጨረሻ እና የድህረ-ምረቃ መርሃ-ግብሮች ተቀብሎ የሚያስተምር ሲሆን፣ የመማር-ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ጎን ለጎን ያከናውናል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለ2019 የትምህርት ዘመንም ከ22 ሺህ በላይ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን ነው የገለጸው።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ለተማሪዎች አቀባበል ልዩ ትኩረት በመስጠትና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁና በእውቀት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት እየሰራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስገዝነት የሚያደርገውን ሽግግር እያጠናቀቀ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የመማር-ማስተማር ሂደቱን በጥራት ለማስኬድ የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
ወደ ራስገዝነት መሸጋገር ተጨማሪ ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ፣ በዕውቀትና በክህሎት የበለጸገ ብቁ ትውልድ ማፍራት የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ታደሰ ሀብታሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪዎች አቀባበል አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አጠናቋል።
በተለይም ከመምህራን ጋር ውይይት በማድረግና የውስጥ አደረጃጀቶችን በማስተካከል፣ ተማሪዎች የትምህርት ዓላማቸውን በብቃት እንዲያሳኩና እርካታቸውን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስገዝነት በሚሸጋገርበት ወቅትም ዋነኛ ትኩረቱ በተማሪዎች ስኬትና በትምህርት ጥራት ላይ እንደሚሆን አክለው ገልጸዋል።
ስለሆነም በምርምር ላይ የተመሰረተ የመማር-ማስተማር ሂደትን በማጠናከር፣ ተማሪዎች ሲመረቁ ለአገሪቱ እድገት የሚመጥን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመን 3 ሺህ 500 አዲስ ተማሪዎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ መመደባቸውን የጠቆሙት ታደሰ(ዶ/ር)፤ ከነባር ተማሪዎች ጋር ሲደመር በአጠቃላይ ከ22 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲው እንደሚከታተሉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከወቅቱ የቴክኖሎጂ ዕድገትና ከሀገሪቱ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ አዳዲስ የድህረ-ምረቃ መርሃ-ግብሮችን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በዚህም ወደ 20 የሚጠጉ የፒኤችዲ እና ሁለት የማስተርስ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት ታደሰ (ዶ/ር)፤ ከእነዚህም መካከል ሳይበር ሴኪዩሪቲ፣ ዳታ ሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
እነዚህ አዳዲስ ፕሮግራሞች ከዓለም አቀፍ የትምህርት ይዘቶችና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተጣጥመው የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ወደ ትግበራ ከመግባታቸው በፊትም የትምህርት ሚኒስቴርን ይሁንታ የማግኘት ሂደታቸው መጠናቀቁን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ዋና ሰብሳቢ ተማሪ ማሩፍ አብዱረህማን እና የሰላም ፎረም ሰብሳቢ ተማሪ አሚር ጂሀድ፤ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በጥሩ ስነ-ልቦና እና መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ጅማ ከተማ የሚገቡ ተማሪዎችን ከከተማው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ቀደም ብሎ በመቀበል ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ የማድረስ ሥራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
ነባር ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ መግባት መጀመራቸውን የጠቀሱት ተወካዮቹ፤ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በጋራ በመቀበል የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል።