የመስቀል እና ኢሬቻ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ስራዎች ሚናቸውን ይወጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል እና ኢሬቻ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ስራዎች ሚናቸውን ይወጣሉ
አዲስ አበባ፣መስከረም 13 /2019 (ኢዜአ):-የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት ሀገራዊ ገጽታን በመገንባትና ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ከእነዚህም መካከል የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ተጠቃሽ ናቸው።
በዓላቱ ከሚኖራቸው ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች ባለፈ ለቱሪዝም ዕድገት እና ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በዓላቱ በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የሚከበሩ መሆናቸውን ተከትሎም፣ የተለያዩ ወጣቶች የበዓላቱን ድምቀት በመጠበቅ፣ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማገዝ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ይስተዋላል።
ዘንድሮ ለሚከበሩት የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትም ወጣቶች የተለመደውን በጎ ተሳትፎ አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርብርሳ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ማህበሩ በቀጣይ በከተማዋ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት በድምቀት ተከብረው እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ለአብነትም የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘታቸውን እንዲሁም እሴቶቻቸውን ጠብቀው በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ለዚህም ማኅበሩ ከ400 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ማከናወኑን አስታውቀዋል።
በዓላቱ የኢትዮጵያን የባህል እሴት በሚመጥን መልኩ በድምቀት ተከብረው እንዲጠናቀቁ በወጣቶች የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት ወጣቶች መካከል ናትናኤል ወጋሶ እንዳለው፣ በዓላቱን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች ደማቅ አቀባበል ለማድረግ እና የበዓላቱን ማክበሪያ ቦታዎች ጽዱ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት አድርገናል ብሏል።
ወጣት እማዋይሽ ጉዲሳ እና ወጣት አላዛር በለጠ በበኩላቸው፣ ሁለቱ በዓላት የጋራ መገለጫዎቻችን በመሆናቸው ለስኬታቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለጹት ወጣቶቹ የመስቀል፣ ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት የጋራ እሴቶቻችን እና የአንድነታችን ማጠናከሪያ መድረኮች መሆናቸውን ተናግረዋል።