ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአንድ ሰው ልትሰጥ የሚገባትን የመጨረሻ ክብር ሰጥታኛለች፣ እኔም ለኢትዮጵያ የሰሰትኩት አንዳች ነገር የለም-የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤መስከረም 12/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአንድ ሰው ልትሰጥ የሚገባትን የመጨረሻ ክብር ሰጥታኛለች፣ እኔም ለኢትዮጵያ የሰሰትኩት አንዳች ነገር የለም ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገላልቻን የሕይወትና የውትድርና ጉዞ የሚዳስሰው "ድል ቁርሱ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ የምረቃ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት የጦር መሪዎችና አባላት ተገኝተዋል።

በስምንት ምዕራፎችና በ355 ገጾች የተቀነበበው "ድል ቁርሱ" (ከኩየራ ወንዞች መሀል የፈለቀው የጦር ሊቅ) በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ እናት ሀገራቸውን ከጠላት ለመጠበቅ የሰጡትን ቁርጠኛ አመራር በድንቅ የሥነ ጽሑፍ ለዛ ይተርካል።

የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ወቅት፤ "በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ በጦርነትና በሌሎች ጉዳዮች እንጂ በራሴ ሕይወት ላይ መጽሐፍ ለማሳተም ፍላጎት አልነበረኝም" ብለዋል።

ይሁን እንጂ መጽሐፉ የእኔ አስተዳደግ ለሚቀጥለው ትውልድ ሞዴል ሊሆን ይችላል በሚል እሳቤ በብዙዎች ጉትጎታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በዚህም ከመጽሐፉ ትውልድ ሀገር ለመገንባት የሚያስችለው መረጃ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

"በበላይ ዘለቀ፣ በአብዲሳ አጋ ሀገር ይገነባል፣ በፊልድ ማርሻል ብርሃኑም ይገነባል፤ ነገር ግን የሆነን ሰው ለማግነንና ለመካብ መሆን የለበትም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአንድ ሰው ልትሰጥ የሚገባትን የመጨረሻ ክብር ሰጥታኛለች፣ እኔም ለኢትዮጵያ የሰሰትኩት አንዳች ነገር የለም በማለት ነው የገለጹት።

መጽሐፉ የነገ መከላከያ መፍጠሪያ ይሆናል፤ ሌሎችም መጻፍ አለባቸው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ሀገር ለመገንባትና ትውልድ ለማሻገር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም