የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በቀጣናው የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን ለመቋቋም ያግዛል- ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በቀጣናው የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን ለመቋቋም ያግዛል- ኢጋድ
ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች በቀጣናው የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም እንደሚያግዙ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ምክትል ዋና ፀሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ ገለጹ።
አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተሞክሮ በመውሰድ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመው እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል።
የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ፤ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች እጅግ የሚያበረታቱ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብት የሚገኙባቸውን መልክአ ምድሮች በመጠበቅ፣ ዛፎችን በመትከል፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሰው እንዲያገሙ እና ውሃን በማሰባሰብ ያከናወነቻቸው ተግባራት በአካባቢ ጥበቃ ቁልፍ የሚባሉ ስራዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
እነዚህ ስራዎች ህብረተሰቡ ንጹህ ውሃ እና ለም መሬት እንዲያገኝ ወሳኝ ሚና አላቸው ያሉት ምክትል ዋና ጸሐፊው፣ በተለይም በተራራማ እና ደጋማ አካባቢዎች የሚከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን በእጅጉ እንደሚቀንሱ አስረድተዋል።
በቀጣናው የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን ለመቋቋም እንደሚያግዙም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በዚህ ስራ ያሳየችው ተነሳሽነት የአጭር ጊዜ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ በረጅም ጊዜ ዘላቂ የአካባቢ ስነ ምህዳር ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
እንደ ምክትል ዋና ፀሐፊው ገለጻ፣ እነዚህ ተግባራት ማህበረሰቡ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን የመቋቋም አቅሙን በማሳደግ፣ ከመሬት መራቆት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ስደትና መፈናቀል ለማስቀረት ያግዛሉ።
የአካባቢ ጥበቃ ከተፈጥሮ እንክብካቤ ባሻገር ዘላቂ የኑሮ መሰረት ለመጣል እና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
የኢጋድ አንዱ ኃላፊነት አባል ሀገራት ልምድና ዕውቀት እንዲለዋወጡ ማድረግ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ፀሐፊው፣ ሌሎች አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ተሞክሮ በመውሰድ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
እነዚህን መልካም ተሞክሮዎች በቀጣናው ማስፋት የአካባቢ ጥበቃን ከማጠናከር ባለፈ፣ ህብረተሰቡ ኑሮውን በዘላቂነት እንዲያሻሻልና ለአየር ንብረት ጫናዎች እንዳይጋለጥ እንደሚያደርግ ገልጸዋል