ከመዋቅራዊ ስብራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና: የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
ከመዋቅራዊ ስብራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና: የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከከባድ መዋቅራዊ ስብራት በመታደግ የረጅም ጊዜ መረጋጋትንና ዕድገትን ለማረጋገጥ የተወሰደ ታሪካዊ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
ሪፎርሙ በሀገሪቱ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ተደቅነው የነበሩ ማነቆዎችን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ለውጦች ተመዝግበዋል።
የሪፎርሙ ዋና ዓላማዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እና የምንዛሬ ተመኑ በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት እንዲወሰን የሚያስችል በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት መዘርጋት ናቸው።
ይህ ማሻሻያ ኢኮኖሚውን ከግዙፍ የመንግሥት መራሽነት ወደ ሕያው የግሉ ዘርፍ መራሽነት በማሸጋገር በምርታማነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማስመዝገብን ያለመ ነው።
ከማሻሻያው ትግበራ ጎን ለጎን፣ በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 158 እና 159 ላይ እንደሰፈረው፤ ማሻሻያው ጊዜያዊ ወጪዎችንና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚያስከትሏቸውን ጫናዎች ለመቋቋም የሚረዳ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲገኝ ተደርጓል። ይህ ዓለም አቀፍ አጋሮች ለኢትዮጵያ ለመስጠት ያቀዱት ትልቁ የተቀናጀ የገንዘብ እርዳታ በመሆኑ ለኢኮኖሚው ሽግግር ትልቅ ትርጉም አለው።
የውጭ ምንዛሬ ገበያን ነፃ ማድረግ እና ተመኑ በገበያ እንዲመራ መደረጉ በጥቁር ገበያ ይካሄድ የነበረውን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በእጅጉ ቀንሶታል።
እንዲሁም ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በቴሌኮም፣ ባንክ፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎች ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያለስጋት እንዲሰማሩ ሰፊ በር ከፍቷል።
ጥብቅ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲዎች መተግበራቸው ቀደም ሲል ከነበረው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ወደ ባለ ነጠላ አሃዝ ዝቅ እንዲል አስችሏል።
በህጋዊ ባንኮች እና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው ሰፊ የምንዛሬ ልዩነት እንዲጠብ በመደረጉ፣ በሕጋዊ መንገድ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ ጨምሮ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል።
ቀደም ሲል አብዛኛው የባንክ ብድር ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን ከፍተኛው የብድር ድርሻ ለግሉ ዘርፍ በመሰጠቱ የምርታማነት አቅሙ በእጅጉ እያደገ መጥቷል።
ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስ እና የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መሆኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የተመዘገቡትን ስኬቶች በዘላቂነት ለማስቀጠል እና ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመከላከል መንግሥት ቁልፍ አቅጣጫዎችን ነድፎ እየሰራ ይገኛል። በበጋ መስኖ ስንዴና በሌማት ትሩፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ማጠናከር፣ እና የዲጂታል ክፍያና የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋፋት የትኩረት ማዕከል ናቸው።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በሪፎርሙ ሳቢያ እንዳይጎዱ የነዳጅና የማዳበሪያ ድጎማዎችን እና የደመወዝ ማሻሻያዎችን በአግባቡ መምራት ሌላኛው የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ነው።
ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪዎችን፣ የምርት መደበቅን እና ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በቁርጠኝነት መከላከል ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ የተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ኢትዮጵያን ከባድ ከመዋቅራዊ ስብራት በመታደግ እና የተረጋጋ የፋይናንስ መሠረት በመጣል ረገድ ታሪካዊ ውጤቶችን አምጥቷል።
ሪፎርሙ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት፣ የምርታማነት አቅምን በማሳደግ እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በቀጣይ የሪፎርም ሥራውን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖውን አጠናክሮ ለመቀጠል የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና የኅብረተሰቡ የተቀናጀ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ አጠቃላይ የለውጥ ጎዳና የብልጽግና ጉዞዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የትግበራ ሂደቱ በግልጽ ያሳያል።