ቀጥታ፡

አቶ ጌታቸው ረዳ ከኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12/ 2019 (ኢዜአ)፦የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ81ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን፣ ከኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቶም ቤረንድሰን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽ ግንኙነት እና የጋራ ትኩረት በሚሹ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ሃሳብ ተለዋውጠዋል። 

አቶ ጌታቸው ረዳ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና፣ በተለይም በሱዳን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን እያደረገች ያለችውን ጥረት አስመልክተው ለኔዘርላንድሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጻ አድርገውላቸዋል።

አንዲሁም  በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድስ መካከል ባለው የሁለትዮሽ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

የኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቶም ቤረንድሰን በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር ለማስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት አጋርነት በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ ለማጠናከር የከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም