የኢትዮጵያ የከፍታና የብልፅግና ጉዞ ህያው ማሳያ - ግብርና - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የከፍታና የብልፅግና ጉዞ ህያው ማሳያ - ግብርና
ግብርና ለዘመናት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶና የሀገራችን የጀርባ አጥንት ሆኖ የዘለቀ ታላቅ ዘርፍ ነው። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የውጭ ምንዛሬ ከመፍጠር ባሻገር፣ ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል በመክፈት ረገድ ዘርፉ የማይተካ አወንታዊ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።
የመደመር መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ልዩ ስትራቴጂካዊ ትኩረት ምርትና ምርታማነትን አዲስ ምዕራፍ ላይ አሸጋግሯል። ሀገራችን ከተረጂነትና ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ወጥታ በራሷ አቅም የምትቆምበትን ራዕይ በአስተማማኝ መሠረት ላይ ጥሎታል።
ለዚህ አጠቃላይ የግብርና ትራንስፎርሜሽንና የከፍታ ምዕራፍ እውን መሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነትና ቀጣይነት ያለው ቀጥተኛ መሪነት የተቀረጹት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ እና ሌማት ትሩፋት ለንቅናቄዎቹ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። እነዚህ ሀገራዊ መርሃ ግብሮች ባህላዊ አሠራርን በዘመናዊ በመተካት፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ኢትዮጵያን የዕድገት ማማ ላይ ያወጡ የስትራቴጂካዊ ለውጥ መደላድሎች ናቸው።
የግብርና ምርታማነትን ያላቁ ቁልፍ ሀገራዊ ንቅናቄዎች
የኢትዮጵያ ግብርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ከባህላዊና ዝቅተኛ አሠራር ተላቆ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ምርታማነትንና የምግብ ሉዓላዊነትን ማዕከል ያደረገ አዲስ ምህዋር ላይ ይገኛል። ይህንን ታላቅ ስልት ወደ ተጨባጭ ውጤት የለወጡት ዋና ዋና ንቅናቄዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነትና መሪነት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ንቅናቄ፣ ሀገራችንን ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ወደ ላኪነት ያሸጋገረ ታሪካዊ ክስተት ነው። ለአርሶ አደሩና ለከፊል አርብቶ አደሩ በተፈጠረ የነቃ ግንዛቤና በተሰጠ መሪነት፣ ከዚህ ቀደም ስንዴ ማብቀል አይቻልም ተብለው ይታሰቡ በነበሩ ቆላማ አካባቢዎች ጭምር ልማቱ በስፋት እንዲያብብ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማው መሬት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የደረሰ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን አልፋ፣ ምርቷን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ ያደረገ ስትራቴጂካዊ ስኬት ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነትና መሪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን ማሳደግና የተራቆቱ መሬቶችን ማገገም አስችሏል። መርሃ ግብሩ የአፈርና የተፈጥሮ ሀብት ጥቃትን ከመከላከል ባለፈ፣ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት በመተከላቸው ለዜጎች ሥነ-ምግብ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ ይህም ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መሆን የቻለና ድንቅ የኢትዮጵያዊያን ተግባር ነው፡፡
የሌማት ትሩፋት
የዜጎችን የተመጣጠነ ምግብ ፍጆታ ለማሻሻልና የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ሌላው ስኬታማ ሀገራዊ ውጥን ነው። በመርሃ ግብሩ የእንስሳት ዝርያን የማሻሻል ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ሲሆን፤ የወተት፣ የሥጋ፣ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የማርና የዓሳ ምርቶች አቅርቦትና ተዳራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ በማድረግ የዜጎችን የተመጣጠነ ምግብ አጠቃቀም አስተማማኝ አድርጎታል።
የኩታ ገጠም እርሻ ስልት
አርሶ አደሮች በጋራና በስፋት እንዲያመርቱ፣ የግብዓት አቅርቦትን በተቀላጠፈ መንገድ እንዲያገኙ እና ዘመናዊ የምርታማነት ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ በማስቻል የዘርፉን ውጤታማነት እያጎለበተ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በኩታ ገጠም እርሻ የሚታረሰው መሬት 13 ሚሊዮን ሄክታር የደረሰ ሲሆን፣ ይህንን ወደ 14 ሚሊዮን ሄክታር ለማሳደግ ግብ ተጥሎ በቁርጠኝነት እየተሰራበት ይገኛል።
ሜካናይዜሽንና የድህረ ምርት እንክብካቤ
ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ በበሬ ሲታረሱ በቆዩ አካባቢዎች ትራክተርንና ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን የመጠቀም ልምድ በግንባር ቀደምትነት እያደገ መጥቷል። በተጓዳኝም የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ዘመናዊ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅና የማቅረብ ሥራ በስፋት በመተግበሩ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የምርት መጠንና ስፋት ዕድገት
በድግግሞሽ አዝርዕትና በዘመናዊ አሠራር አማካኝነት የታረሰው መሬት መጠን ወደ 33 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማድረስ ተችላል። በ2018 ዓ.ም የምርት ዘመን ብቻ 1 ነጥብ 85 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉ የዘርፉን አጠቃላይ የዕድገት ጉዞ በጉልህ ያሳያል።
መደምደሚያ
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ግብርና እያስመዘገበ ያለው አጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጥና ዘላቂ ዕድገት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነትና በዜጎች ትልቅ ትብብር የተገኘ ታሪካዊ ውጤት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነደፏቸው የልማት ንቅናቄዎች ግብርናውን ዘርፍ በመለወጥ ከተረጂነት አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ አውጥተው ወደ ሀገራዊ ብልፅግና፣ ራስን የመቻል አቅም እና የምግብ ሉዓላዊነት ጎዳና መምራት ችለዋል።
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው ይፋዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) ከ30 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። በግብርናው እሴት ሰንሰለት ውስጥ ለ65 በመቶ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ገንብቷል። እነዚህ አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡት የልማት ውጥኖቹ የኢትዮጵያን የከፍታና የብልፅግና ጉዞ እውን እያደረጉት ለመሆናቸው ህያው ማረጋገጫዎች ናቸው።