ቀጥታ፡

"ድል ቁርሱ" መፅሐፍ የወታደራዊ ታሪክ የምርምርና የመማሪያ ሰነድ ሆኖ የሚያገለግል ነው - ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/ 2019(ኢዜአ)፦"ድል ቁርሱ" መፅሐፍ የወታደራዊ ታሪክ የምርምርና የመማሪያ ሰነድ ሆኖ የሚያገለግል ነው ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለፁ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገላልቻን የሕይወትና የውትድርና ጉዞ የሚዳስሰው "ድል ቁርሱ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ የምረቃ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።

በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል መኮንኖች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በስምንት ምዕራፎች በ355 የተቀነበበው "ድል ቁርሱ" (ከኩየራ ወንዞች መሀል የፈለቀው የጦር ሊቅ) በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ እናት ሀገራቸውን ከጠላት ለመጠበቅ የሰጡትን ቁርጠኛ አመራር በድንቅ የሥነ ፅሁፍ ለዛ ይተርካል።

በምረቃው ላይ የታሪክ ተመራማሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ጥልቅ ዳሰሳ አቅርበዋል።

በዚህም "ድል ቁርሱ" መፅሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሕይወት ታሪክና ትዝታ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ወታደራዊ የታሪክ ድርሰትና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ያለውን ትልቅ ክፍተት የሚሞላ ሲሉ ገልፀዋል።

መጽሐፉ የፊልድ ማርሻሉን የግል የሕይወት ታሪክና የተጓዙበትን የለውጥ ሂደት ከማሳየቱም በላይ፣ በየምዕራፉ ለሀገርና ለነፃነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ሁሉ ትልቅ መታሰቢያ መሆኑን ተናግረዋል።

በወታደራዊው ዘርፍ በርካታ የታሪክ አጋጣሚዎች ሳይመዘገቡና ሳይሰነዱ የሚቀሩ በመሆናቸው፣ ይህ መጽሐፍ ከተካተቱት በርካታ የታሪክ አጋጣሚዎችና ፎቶግራፎች ጋር ተያይዞ ለወደፊቱ ትውልድ ትልቅ የምርምርና የመማሪያ ሰነድ ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል።

መጽሐፉ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን የሕይወትና የወታደራዊ ተሳታፊነት በሦስት ሥርዓታት ውስጥ ያለፉበትን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም የሀገር ፍቅርና ወታደራዊ ሳይንስን አጣጥመው የሄዱበትን መንገድ በሰፊው የሚተነትን እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም