"ድል ቁርሱ" መጽሐፍ አንድ ከኩየራ የተነሳ ወጣት የደረሰበትን የህይወት ውጣ ውረድ መዳሰስ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካና ወታደራዊ ታሪክ ያለው ነው - ኢዜአ አማርኛ
"ድል ቁርሱ" መጽሐፍ አንድ ከኩየራ የተነሳ ወጣት የደረሰበትን የህይወት ውጣ ውረድ መዳሰስ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካና ወታደራዊ ታሪክ ያለው ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/ 2019(ኢዜአ)፦በኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሕይወት ዙሪያ የተሰነደው "ድል ቁርሱ" መጽሐፍ አንድ ከኩየራ የተነሳ ወጣት የደረሰበትን የህይወት ውጣ ውረድ መዳሰስ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካና ወታደራዊ ታሪክ ያለው መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።
በመርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት የጦር መሪዎችና አባላት ተገኝተዋል።
በስምንት ምዕራፎች በ355 የተቀነበበው "ድል ቁርሱ" (ከኩየራ ወንዞች መሀል የፈለቀው የጦር ሊቅ) በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ እናት ሀገራቸውን ከጠላት ለመጠበቅ የሰጡትን ቁርጠኛ አመራር በድንቅ የሥነ ፅሁፍ ለዛ ይተርካል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የጦር ጄኔራሎች ፅሁፎች የሀገርና የትውልድ ልዕልና የሚቀርጹና የሚሰንዱ ዶሴዎች ናቸው።
አንድ ታዳጊ ፊልድ ማርሻል ለመሆን ቢፈልግ "ድል ቁርሱ" መፅሀፍ ትልቅ ሞዴል እንደሚሆነው ጠቅሰው፤ መጽሐፉ ለሚቀጥለው ትውልድ ያልተላለፉ የሀገር ታሪክና የወደፊት መዳረሻን ለመተለም መነሻ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ጀግኖችን የሚያከብር ህዝብ የታሪክ ባለቤት፣ ጀግናውን የሚረሳ የጠላት ምርኮኛ ይሆናል ብለዋል።
መጽሐፉ ሀገረ መንግስት ለማፅናትና ትውልድ ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ሀያሲ ብርሀኑ ደቦጭ በበኩላቸው፤ በኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሕይወት ዙሪያ የተሰነደው "ድል ቁርሱ" መጽሐፍ ለሰራዊት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
መጽሐፉ የሰራዊቱን ዕድገት ያሳያል ያሉት ሀያሲ ብርሀኑ ደቦጭ፤ በመሰረታዊ ወታደር፣ ኮማንዶና አየር ወለድ ያለፉበትን ውጣ ውረድ እንደሚያንጸባርቅ ገልጸዋል።