"ድል ቁርሱ" መፅሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን እውነተኛ የሀገር ፍቅር እና የነፃነትና መብት ማስከበር ጥረትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው - ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
"ድል ቁርሱ" መፅሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን እውነተኛ የሀገር ፍቅር እና የነፃነትና መብት ማስከበር ጥረትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው - ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ "ድል ቁርሱ" መፅሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን የንባብ ባህል፣ እውነተኛ የሀገር ፍቅር እና የነፃነትና መብት ማስከበር ጥረትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው ሲሉ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ገለፁ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገላልቻን የሕይወትና የውትድርና ጉዞ የሚዳስሰው "ድል ቁርሱ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ የምረቃ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል መኮንኖች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በስምንት ምዕራፎች በ355 የተቀነበበው "ድል ቁርሱ" (ከኩየራ ወንዞች መሀል የፈለቀው የጦር ሊቅ) በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ እናት ሀገራቸውን ከጠላት ለመጠበቅ የሰጡትን ቁርጠኛ አመራር በድንቅ የሥነ ፅሁፍ ለዛ ይተርካል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ጥልቅ ዳሰሳ ያቀረቡ ሲሆን፤ በዳሰሳቸው ወቅት የመጽሐፉን ስነ-ጽሑፋዊ ይዘት፣ የወታደራዊ ሕይወት ገጽታዎችን እና የፊልድ ማርሻሉን የፖለቲካ ፍልስፍና በዝርዝር አብራርተዋል።
በዚህም መጽሐፉ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ታሪክ በከፍተኛ የስነ-ጽሑፍ ጥራት መጻፉን ገልፀዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገና በ18 ዓመታቸው ከአዛዡ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም ጋር ያደረጉትን ውይይት፣ ያሳዩትን ንቃትና ቅልጥፍና፣ እንዲሁም የአየር ወለድ ስልጠና የነበረውን ጥብቅ ዲሲፕሊንና ለሀገር መቆምን መጽሐፉ በግልጽ እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።
በአውዳሚ ጦርነቶች ያጋጠሟቸውን እንደ አባቶችና ገበሬዎች ያሉ አጋዥ ሰዎችን፣ የሌሎችን አየር ወለድ ጀግኖች ታሪክ፣ እንዲሁም የእርሳቸውን እውነትን ፊት ለፊት የመናገር ባህሪና አቋማቸውን እንዳብራራም ተናግረዋል።
በፖለቲካና በውትድርና ጉዟቸው ወቅት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም የፀኑበት አቋም በግልፅ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በከባድ የፖለቲካ ውሳኔዎች ወቅት የነበራቸውን ጥልቅ ሀሳብ መርህ ያገናዘቡ መሆናቸውን እና ምንም ዓይነት ዋጋ ቢያስከፍለኝ ለህዝቤና ለሀገሬ መቆም አለብኝ በሚል የወሰዱትን አቋም የሚያንፀባርቅ መፅሀፍ ነው ብለዋል።
መጽሐፉ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን የንባብ ባህል፣ እውነተኛ የሀገር ፍቅር እና የነፃነትና መብት ማስከበር ጥረትን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።