ቀጥታ፡

በአስተዳደሩ የተዘረጋው የዲጂታል አሠራር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስችሏል

ድሬደዋ፣ መስከረም 12/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር የተዘረጋው የዲጂታል አሠራር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ለመፍታት ማስቻሉ ተገለፀ።

በድሬደዋ አስተዳደር የተገልጋዮችን ቅሬታና አቤቱታ ለመፍታት በተዘረጋው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሠራር ላይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና ተሰጥቷል።


 

በወቅቱም የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሰዓዳ አዋሌ እንደገለጹት፤ በአስተዳደሩ የተዘረጋው የዲጂታል አሠራር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ለመፍታት አስችሏል።

ዘመናዊ የዲጂታል አሠራሩ በከንቲባው ጽሕፈት ቤት የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ዳይሬክቶሬት ሥር በሚገኙ ተቋማት ተተግብሮ ውጤታማ መሆኑንም አስረድተዋል።

በከንቲባው ጽሕፈት ቤት የተገኘውን ውጤት ሕዝብ በብዛት በሚገለገልባቸው የወረዳ ተቋማት ውስጥ ለማስጀመር የዛሬው ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ሥልጠናው የዲጂታል አሠራሩን በዚህ ሳምንት በሁሉም ወረዳዎች ለማስጀመር ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በገጠር ክላስተሮች እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

የዲጂታል አሠራር መተግበሪያውን አስተዳደሩ  ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ለተለያዩ ተቋማት እያበለጸገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ቅሬታ፣ አቤቱታና ሥልጠና ቡድን መሪ አቶ አሻግሬ ታደሰ በበኩላቸው፤ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የበለጸገው ዲጂታል መተግበሪያ የሕዝብን ቅሬታ በፍጥነት ለመፍታት ማገዝ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የዲጂታል አሠራሩ በየደረጃው የሚገኘው አመራር የሚቀርቡለትን የትኛውንም ቅሬታዎች ባለበት ቦታ ሆኖ በፍጥነት ለመመለስ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

በሶፍትዌር አተገባበሩ ላይ የተሳተፉት ሰልጣኞች በበኩላቸው፤ ሥልጠናው የዲጂታል አሠራሩን በፍጥነት ወደ ተግባር በማውረድ የተሻለ አገልግሎትን ለነዋሪው ለመስጠት እንደሚያግዛቸውም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም