ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ በንቃት ትሳተፋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ በንቃት ትሳተፋለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12 /2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በ81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ በንቃት እንደምትሳተፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጠቅላላ ጉባኤው በኒው ዮርክ “መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መፍጠር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።
በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ እና ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ተወካዮች በልዑካን ቡድን ውስጥ ተካተዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላላ ጉባኤው እና የሀገራት መሪዎች ንግግር በሚያደርጉት የከፍተኛ ደረጃ የምክክር ሳምንት ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁና በአፍሪካ ፍላጎቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በበርካታ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ስብሰባዎች ላይ እንደምትሳተፍም ሚኒስቴሩ ገልጿል።