የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን የሕይወትና የውትድርና ጉዞ የሚዳስሰው "ድል ቁርሱ" መጽሐፍ የምረቃ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን የሕይወትና የውትድርና ጉዞ የሚዳስሰው "ድል ቁርሱ" መጽሐፍ የምረቃ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገላልቻን የሕይወትና የውትድርና ጉዞ የሚዳስሰው "ድል ቁርሱ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ የምረቃ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል መኮንኖች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በስምንት ምዕራፎች በ355 የተቀነበበው "ድል ቁርሱ" (ከኩየራ ወንዞች መሀል የፈለቀው የጦር ሊቅ) በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ እናት ሀገራቸውን ከጠላት ለመጠበቅ የሰጡትን ቁርጠኛ አመራር በድንቅ የሥነ ፅሁፍ ለዛ ይተርካል።
ጸሐፊው በአማን ታደሠ በድርሰቱ "ከኩየራ ወንዞች መሀል ፈልቀው፣ የመከላከያ ሠራዊታችንን ወደ ከፍታ ማማ ያሸጋገሩ የጦር ሊቅ" ሲል ጀብዳቸውን ይተርካል።
የድል ቁርሱ መጽሐፍ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በደረሰው ጥቃት በመረጃም በመሳሪያም የተዳከመውን የሰራዊት አባል በማሰባሰብና አመራር በመስጠት የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን ይዳስሳል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ የተበተነን ሰራዊት እንደገና መገንባት ከባድ ቢሆንም በተግባር አድርገው ለኢትዮጵያ ህዝብ ድል አብስረዋል።
ከአዲስ አበባ እስከ ደብረ ሲና፣ ከባህር ዳር እስከ ጋሸና፣ ከወልቃይት እስከ አፋር በተለያዩ የጦር ግንባሮች በስፍራው በመገኘት ሰራዊቱን በማበርታት ለድል ማብቃታቸው ጸሀፊው በማጣቀሻዎች ያብራራል።
ጸሀፊው ወደ ኋላ መለስ ብሎ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑን የጀግንነት ታሪክና የጦር ሜዳ ውሎ ይተርካል፤ ከመሰረታዊ ወታደር አስከ መስመራዊ መኮንን የፈፀሟቸውን ገድሎች በታሪክ መነፅር ያስቃኛል።
የኢትዮጵያ ግዙፉ ጦር መሪ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለሀገራቸው በሰሩት ጀብዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ሜዳይ ተበርክቶላቸዋል።
"ድል ቁርሱ" (ከኩየራ ወንዞች መሀል የፈለቀው የጦር ሊቅ) በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑን የወጣትነት፣ የፍቅርና የትዳር ሕይወት እንዲሁም በሀገሪቷ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ውስጥ ያለፉባቸውን ጉልህ ኹነቶች በስፋት የዳሰሰ ነው።
በተጨማሪም መጽሐፉ የአንድን ወታደራዊ መሪ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውና የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን፣ ታላላቅ የፈተና ተራሮችንና ተግዳሮቶችን ለማለፍ የተደረጉ ጽናቶችን የሚዳስስ ሲሆን፤ እንዲሁም ለተኪው ትውልድ የሚተላለፉ የታማኝነትና የመሪነት ፈለጎችን አካቷል፡፡