በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብና እርጥበት ይኖራል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብና እርጥበት ይኖራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብና እርጥበት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በሚቀጥሉት ቀናት በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የአፈር ውስጥ እርጥበት ይኖራል።
በተመሳሳይ በሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀላል መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖርና በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ተፋሰሶች ላይ ደግሞ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው የገጽ ምድር የውኃ ፍሰት እንደሚኖር መግለጫው ጠቅሷል።
ምዕራብ ወለጋ፣ ኢሉባቦር፣ አርሲ፣ አብዛኞቹ የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብ፣ መካከለኛ፣ ደቡብ እና ሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን፣ የምዕራብ እና የምስራቅ ጎጃም፣ አዊ፣ ማኦ ኮሞ፣ ምዕራብ ኦሞ እና አሶሳ ከመካከለኛ እስከ ከባድ እርጥበት የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ደቡብ እና ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ ማረቆ ልዩ ወረዳ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ የሲዳማ ሁሉም ዞኖች እና የወላይታ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ እርጥበት የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
ይህ የአየር ሁኔታ የአፈር እርጥበትን ለማሻሻል፣ ለረጅም እና መካከለኛ ጊዜ ሰብሎች እድገት እንዲሁም ዘግይተው ተዘርተው በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎች ፍሬያማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ለቋሚ ተክሎች ልምላሜ፣ ለእንስሳት መኖና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት መጎልበት እንዲሁም የዝናብ ውኃን አሰባስቦ ለማስቀረት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።
የመኸር ሰብል አብቃይ አከባቢዊች አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ምርታማነትን ለመጨመር የሰብል በሽታና አረምን አስቀድመው እንዲከላከሉ፤ ፀረ-አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችንም የግብርና ባለሙያዎችን በማማከር ብቻ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።
የውኃ ትነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የግብርና ስራዎችን ማከናወን፣ የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ ለልማት ማዋል፣ ለእንስሳት ግጦሽ ሳርን በተቆጠበ መንገድ መጠቀም እና የዝናብ ውኃን አጠናክሮ ማከማቸት እንደሚገባ መክሯል።