ሕገ-ወጥ ንግድ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመከላከል የተቋማት ትብብርን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ-ወጥ ንግድ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመከላከል የተቋማት ትብብርን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመከላከል በተቋማት መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) ገለጹ።
ይህ የተገለጸው በምስራቁ የንግድ ኮሪደር ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል ዓላማ በማድረግ በተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ ነው።
በውይይቱ ላይ የፌዴራል፣ የክልሎች፣ የከተማና የዞን አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ሀገሪቱ የጀመረችውን ሁሉን አቀፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኤክስፖርት ተወዳዳሪነት እና የኢንዱስትሪ ሽግግር ሙሉ በሙሉ ከግብ ለማድረስ ሕገ-ወጥ ንግድን በጋራ መከላከልና ሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴን ማበልጸግ ይገባል ብለዋል፡፡
ሕገ-ወጥ ንግድ በመንግሥት መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ በእጅጉ በመጎዳት ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሌሎች የልማት ስራዎች ሊውል የሚችል ሀብት እንዲባክን እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
በተለይም የምሥራቁ የንግድ ኮሪደር የአገር ውስጥ ገበያን ከዋና ዋና የንግድና የድንበር መስመሮች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቁመዋል።
ሕገ-ወጥ ንግድን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከልም በፌዴራል ተቋማት፣ በክልል የንግድ ቢሮዎች፣ በጉምሩክ፣ በሕግ አስፈጻሚዎች እና በግሉ ዘርፍ መካከል የተጠናከረ የትብብር ሥርዓትን ማጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም መዋቅሮችን በተሻለ መልኩ መጠቀም፣ ግልጽ የመገናኛ መስመሮችን ማዘጋጀት እና መደበኛ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንዲሁም ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና ተጨባጭ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማንሸራሸር የተቀናጀ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የሁሉም ዜጋና ተቋማት የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቴክኒክና ከአሰራር አንጻር የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በየጊዜው እየፈተሹ ማስተካከል እንደሚገባ የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፤ አምራቾች ምርታማነትን በማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።