ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የገጠርና የከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀምን በማሻሻል ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል

ጎንደር፤መስከረም 12/2019(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የገጠርና ከተማ የመሬት ሀብትን አያያዝና አጠቃቀምን በማሻሻል ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ መሬት ቢሮ ገለፀ።  

የጎንደር ከተማ መሬት መምሪያ ከዘርፉ  ባለሙያዎች፣ ከዳኞች እና ከአጋር ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ ዛሬ አካሄዷል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዕብሬ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በገጠርና በከተሞች የመሬት ሀብትን መዝግቦ ከመያዝ፣ የአጠቃቀም ሥርዓትን ከማስተካከልና የይዞታ ማረጋገጫ ከመስጠት አንጻር ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።

ከዚህ ውስጥም በገጠር አካባቢ የተሠሩ ሥራዎች የኢኮኖሚ ጠቃሚነትን ከማሳደግ ባለፈ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የፍርድ ቤት ክርክሮችን ለመቀነስ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ የይዞታ ማረጋገጫውን በማስያዝ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን ነው የገለጹት።

በክልሉ  ላለፉት ዓመታት የይዞታ ማረጋገጫና የምዝገባ ሥራዎች በ14 ከተሞች ላይ ብቻ ይካሄድ እንደነበር ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ተጨማሪ 66 አዳዲስ ከተሞችን ለማካተት ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

በተለይም በከተሞች የሚስተዋለውን የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ይበልጥ ለማሻሻል በየከተሞቹ ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመሬት ሥርዓትን ማስተካከል፣ አጠቃቀሙን መወሰንና የገጠር ኮሪደር ልማትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ኃላፊው አስታውቀዋል።


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ ትዛዙ በጽሐ በበኩላቸው፤ በከተማው ዘመናዊ የመሬት ሥርዓት በመዘርጋት ለ36 ሺህ 953 ባለይዞታዎች የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቷል ብለዋል። 

በ2018 በጀት ዓመት የይዞታ ወሰን መጋፋትና የካርታ መደራረብ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስተካከል የ7 ሺህ ባለይዞታዎችን መረጃ ወደ ሲስተም በማሸጋገር አገልግሎት መስጠት መቻሉንም ገልጸዋል።

በአዲሱ የ2019 በጀት ዓመት ከወረቀት አሠራር ሙሉ በሙሉ በመውጣት አገልግሎቶችን በሲስተም መስጠት ዋና ትኩረት መሆኑን ጠቁመው፣ የከተማና የገጠር ካዳስተር ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የከተማውን ማስተር ፕላን ከማስጠበቅና ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ከመከላከል አንጻር ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን የተናገሩት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ ናቸው።


 

በከተማው በሕገ-ወጥ መንገድ ተገንብተው የነበሩ ከአራት ሺህ በላይ ሼዶችን ማንሳት መቻሉን ጠቅሰው፤ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራንና ያልተፈቀዱ የቤት ግንባታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል የካዳስተር ሥራዎችን የማፋጠን ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም